የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች ማህበር በመንግስት በሚከወኑ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉ እየተደረጉ አይደለም አለ፡፡
በዚህም ምክንያት ‘’የሃገር ውስጥ ተቋራጮች ስራ አጥተዋል’’ ያለ ሲሆን ‘’በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚከወኑ ፕሮጀክቶችም ተሳትፎቸው አነስተኛ ነው’’ ብሏል፡፡
‘’የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን መብት ለማስከበር የሚያግዝ ህግ ቢኖርም ህጉ እና መመሪያው እየተተገበረ አይደለም’’ ብሏል ማህበሩ።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማርያም ‘’ከአዲስ አበባ ባለፈ በሀገር ውስጥ የሚከወኑ የልማት ስራዎች የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉ በህግ ቢቀመጠም ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች የሚሰጠው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ ህጉ የሚፈቅደልንን መብት እየተከበረልን አይደለም’’ ብለዋል።
የሀገር ዉስጥ ተቋራጮችን ለማበረታታት ህግ ቢወጣም የአተገባበር ክፍተት በመኖሩ አብዛኞቹ ተቋራጮች ስራ እያጡ መሆኑን አቶ ግርማ ነግረውናል።
በዚህም የሀገር ውስጥ ሀብትን የመጠቀም መብታቸው ተነፍጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ያነሳውን ቅሬታ በተመለከተ የሚመለከተውን አካል አነጋግረናል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ ቤት ሀላፊ አቶ ሰኚ ክፍሌ በከተማዋ የሚገነቡ ትላልቅም ሆኑ አነስተኛ ፕሮጀክቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለሃገር ውስጥ ተቋራጭ የተሰጡ ናቸው ይላሉ።
አያይዘውም የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ቁጥር እና በፕሮጀክቱ የተሳተፉት ላይመጣጠን ይችላል እሱም ከፕሮጀክቱ ውስንነት አኳያ ነው ሲሉም ነግረውናል።
ፍቅሩ አምባቸው
Comments