የሰላም እጦት በመኖሩ ህጋዊ የዱር እንስሳት አዳኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ተባለ፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በህጋዊ መንገድ የዱር እንስሳትን ለሚያድኑ ሰዎች ህጋዊ ፍቃድ ትሰጣለች በዚህም በሚልዮን የሚቆጠር ብር ታገኝበታለች፡፡
አሁን ላይ 4 ክልሎች ውስጥ በህጋዊ መንገድ ፍቃድ ተወስዶ የዱር እንስሳት አደን የሚፈፀም ሲሆን ሀገሪቱ ላይ ባለው የሰላም እጦት ምክንያት እነዚህ ቦታዎች አዳኝ እያጡ መሆኑን ሰምተናል፡፡
የዱር እስሳት ጥበቃ ባለስልጣናት እንዳለው ከዚህ በፊት በዓመት ከ35 እስከ 50 የዱር እንስሳት አዳኝ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር፡፡
በ2015 ዓ.ም 37 የሚሆኑ አዳኞች መጥተው የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ይህ ቁጥር አሽቆልቁሎ ወደ 28 ዝቅ ብሏል፡፡
በዚያው ልክ የሚገኘው ገቢም ቀንሷል ያሉን በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ቀርቁ ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት የዱር እንስሳት የማደኛ ዋጋ አለማሻሻሏን የነገሩን አቶ ዳንኤል በአለማቀፍ መስፈርት መሰረት አንድ ሀገር በየ10 ዓመት የዱር እንስሳት አደን ዋጋ ማሻሻል እንደምትችል ነግረውናል፡፡
አሁን እንዲሻሻል የተጀመረው ስራ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አልጸደቀም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዱር እንስሳት ህጋዊ አደን ዋጋ ከ50 ዶላር እስከ 15,000 ዶላር እንደሚደርስም ሰምተናል፡፡
በአደን ወቅት ወጣት እና ሴት የዱር እንስሳት ማደን ክልክል ነው ያሉት ኃላፊው ይህ ተፈፅሞ ሲገኝ አዳኙ ለእንስሳው የሚከፈለው ዋጋ እጥፉን ይከፍላል ተብሏል፡፡
ህገ-ወጥ አዳኝ ከሆነ ከገንዘብ ቅጣት ባሻገር እስራት ይጠብቀዋል ይላሉ አቶ ዳንኤል፡፡
አሁን ባለው ጦርነትና የሰላም እጦት በተለይም በኦሮሚያ ክልል የአደን ስፍራዎች ላይ ስራ ለመስራት ተቸግረናል ያሉት አቶ ዳንኤል የውጪ አዳኞች ቅድሚያ ሰላም ይፈልጋሉ ይህ ከሆነ እንደ ቀድሞ የሻለ የአዳኝ ቁጥር ማግኘት ይቻላል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለሕጋዊ አደን ከተፈቀዱ የዱር እንስሳት መካከል አንበሳ፣ ነብር፣ የደጋ አጋዘንን ጨምሮ በአጠቃላይ 54 የዱር እንስሳት ለአደን ሲሆኑ እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ተኩላ ጨምሮ 48 የዱር እንስሳት ደግሞ ለአደን ከተከለከሉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው መባሉን ሰምተናል፡፡
በረከት አካሉ
Comments