በተለያየ ጊዜ የንፁሃን ዜጎች አፈና እና ዕገታ ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ድርጊቱን ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ብሏል።
ክልሉ እንዳለው በዚህ አይነቱ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ከጥፋት ተግባራቸው ታቅበው ወደ ሠላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው፤ እምቢ ባሉት ላይ ደግሞ የሃይል እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል።
በሌላ በኩል ከቀናት በፊት ከታገቱ 167 የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 160ዎቹ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ነጻ መውጣታቸውን ክልሉ ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የሰዎችን አፈና እና ዕገታ የተመለከቱ ዜናዎች በየጊዜው በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው፡፡
አቅም ያለው ገንዘብ እየከፈለ ከዕገታው ነፃ ሲሆን ይህን ማድረግ ያልቻለ ደግሞ በህይወት ከቤተሰቡ መቀላቀል አስቸጋሪ ሆኖበት ይታያል።
እንዲህ አይነቱ የዕገታ እና አፈና ተግባር ከሚፈጸምባቸው አካባቢዎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው።
በአብዛኛው ተግባሩን የሚፈጽመው ‘’ሸኔ’’ ብሎ የሚጠራው ቡድን እንደሆነ የሚገልጸው የክልሉ መንግስት፤
ሁኔታውን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑ ይናገራል።

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ፤ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃት በማቆም ወደ ሠላማዊ ኑሮ እና የፖለቲካ ትግል የመቀላቀል ፍላጎት ያላቸውንም ሰዎች፤ ረጅም ርቀት ተጉዘን እየተቀበልናቸው ነው ሲሉ አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።
በሰዎች ላይ እገታ እና አፈና እየፈጸመ ያለው ቡድን አሁን ላይ መዳከሙንም ሃላፊው የተናገሩት።
በሌላ በኩል ከቀናት በፊት ከዳባርቅ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተመለሱ በነበረበት ወቅት፤ ከታገቱ 167 ተማሪዎች 160ዎቹ መለቀቃቸውን አቶ ሃይሉ ነግረውናል።
አሁንም በዕገታ ስር የሚገኙ ቀሪ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የፀጥታ ሃይሎች ጥንቃቄ የታከለበት እርምጃ እየወሰዱ ሲሆን ታጋቾቹን በማስለቀቁ ሂደት የተጎዳ ተማሪ እንደሌለም አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።
ቀሪ ታጋቾችን የማስለቀቁ ግዳጅ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ መረጃ እንደሚሰጥም አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ… https://shorturl.at/qWPuY
ንጋቱ ረጋሣ
Comentários