top of page

ሐምሌ 3፣ 2016 - ብሔራዊ ባንክ  በማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፍ  አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማእቀፍ ይፋ ማድረጉ ተሰማ

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ  በማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፍ የሚታዩ ስር የሰደዱ ድክመቶችን ለማስወገድ ያግዘኛል ያለውን አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማእቀፍ ይፋ ማድረጉ ተሰማ።


ይህ ለውጥ በኢትዮዽያ  የማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፍ የሚታዩ አንዳንድ ስር የሰደዱ ድክመቶችን ለማስወገድ ይረዳል ተብሏል።


ባንኩ የዋጋ መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስፈን ማእከላዊ ባንኩ አብዛኛዎቹ የአለም ሀገራት ወደሚጠቀሙበት በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማእቀፍ በዚህ አመት እንደሚሸጋገር ተናግሮ ነበር።


በዚህም መሰረት ብሔራዊ ባንኩ ለሽግግሩ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን በአብዛኛው አጠናቆ ዛሬ አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች ይፋ አድርጔል።አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ 6 የውሳኔ ነጥቦችን ይዘዋል።


በአንደኛ ደረጃ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሰረተ ፖሊሲ እንደሚሸጋገር ገዥው አረጋግጠዋል።


በዚህ በአዲሱ የገንዘብ የፖሊሲ ማእቀፍ መሰረት ባንኩ በዋናነት የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማሳየትና አጠቃላይ የገንዘብና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የብሔራዊ ባንክ ተመን የሚባለውን የፖሊሲ ተመን ይጠቀማል ተብሏል።


ይህ የወለድ ተመን እንደ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ሁኔታ እየታየ ከፍ ወይም ዝቅ የሚል ይሆናል።


በሁለተኛ ደረጃ የብሔራዊ ባንክ የወለድ ተመን ለመጀመርያ ግዜ 15 በመቶ ይሆናል መባሉን ገዥው አረጋግጠዋል።ይህ የፖሊሲ ተመን አሁን የሚታየውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ተብሏል።


ይህ የፖሊሲ ተመን ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ ተመን እንደማይመለከት ባንኩ አሳስቧል።


ባንኮች በውድድር ላይ ተመስርተው ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል።


አሁን ባንኮች በቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ዝቅተኛው የ 7 በመቶ ወለድ በዚህ የፖሊሲ ተመን ምክንያት ለውጥ እንደማይደረግበት በብሔራዊ ባንክ ተናግሯል።


በሶስተኛ ደረጃ ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንት ያካሂዳል ተብሏል።


ይህ ጨረታ የሚደረጉት ባንኩ ከወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ከባንክ ስርአት ውስጥ ትርፍ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲያስችለው መሆኑ ተሰምቷል።


እነዚህ ጨረታዎች የሰነዶች ግብይት በመባል ይታወቃሉ።


በባንክ ስርአት ውስጥ ያለአግባብ የተከማቸ የገንዘብ መጠን ሲኖር ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ስርአቱ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሰነዶች ግብይት ጨረታ ያካሂዳል ተብሏል።


በአራተኛ ደረጃ ለባንኮች የአንድ ቀን የብድር አገልግሎትና የአንድ ቀን የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት ይሰጣል።


ይህ አገልግሎት ባንኮች በአንድ ቀን ውስጥ የገንዘብ አቋማቸውን ለማስተካከል እንዲረዳቸው የታሰበ የገንዘብ ፖሊሲ ነው።

እነዚህ ቋሚ የፖሊሲ አገልግሎቶች የሚሰጡት ከብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን 3 በመቶ በማስበለጥ ወይም በማሳነስ እንደሚሆን ገዥው አስረድተዋል።


በአምስተኛ ደረጃ ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበትን የተነቃቃ የገንዘብ ገበያ ለመመስረት የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርአት በቅርቡ ለማቋቋም ስንዱ መሆኑ ተነግሯል።


ይህ ገበያ በኤሌክትሮኒክስ ስርአት ተመስርቶ በሚገባ በስራ ሲውል ትርፍ ገንዘብ ያላቸው ባንኮች የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው ባንኮች ማበደር  ያስችላቸዋል።


ይህ አሰራር ወደ ስራ ሲተረጎም የባንክ ለባንክ የወለድ ተመን ከማእከላዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን የሚጣጣም ነው።


ይህ ካልሆነ ግን ብሔራዊ ባንክ ሁኔታውን ለማስተካከል የሰዶች ግብይት ጨረታን እንደሚጠቀም ገዥው አረጋግጠዋል።


በስድስተኛ ደረጃም የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ ወደ አዲሱ የገንዘብ ማእቀፍ ሲሸጋገር በሽግግር ወቅት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩት ቀጥታ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች በግዚያዊነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል።


ገዥው ዛሬ ይፋ የተደረገውን ለውጥ  የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ በማዘመን አሰራሩን ከአለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር እንዲሰለፍ የሚያስችል ታሪካዊ እርምጃ ነው ብለውታል።አምና ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ የባንክ የብድር እድገትን በተወሰነ ደረጃ የሚገታ እና የመንግስት የቀጥታ ብድርን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።


በዚህም ምክንያት የዋጋ ንረቱን በማረጋጋት አወንታዊ ውጤት መገኘቱን የብሔራዊ ባንከ ገዥው ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።


የብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በአመቱ መጨረሻ ከ 20 በመቶ በታች ለማድረስ ያስቀመጠው እቅድ ተሳክቷል ተብሏል።


ተህቦ ንጉሴ

Comments


bottom of page