ሐምሌ 3፣ 2016 - መንግስት በየቦታው የሚፈፀሙ እገታዎችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ፡፡
- sheger1021fm
- Jul 10, 2024
- 1 min read
እተፈፀሙ ያሉ እገታዎች የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት እየገደቡ መሆኑንና በሰላም ወጥቶ መግባት ቅንጦት እየሆነ መምጣቱን የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለሸገር ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የቅድሚያ ቅድሚ ሃላፊነቱና መንግስት የሚያሰኘው ተግባር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆን ሲገባው ይህ እየሆነ አለመሆኑ ያሳስበናል ያሉት አቶ ደስታ፤ አሽከርካሪዎች፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ሰዎች እንዲሁም ተማሪዎች በሚፈፀምባቸው እገታ ወጥተው እየቀሩ ነው፣ስለዚህም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በየስፍራው የሚፈፀሙ እገታዎችን እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡
ማስቆም ካልቻለም አለመቻሉን ለህዝቡ ያሳውቅ ብለዋል ሰብሳቢው፡፡
ሰዎችን እያገቱ የቤዛ ክፍያ መጠየቅን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ያወጡት መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲ በንፁሃን ሰዎች ላይ የሚፈፀመውን እገታ አውግዘዋል፡፡
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደሰፈረው በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ዋና ዋና ወንጀሎችን ዘርዝሯል፡፡

ከነዚህም ውስጥ "በአስገዳጅ ሁኔታ ሰውን የመሰወርና ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶች" በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
መንግስት እነዚህ ወንጀሎች መፈፀማቸውን እያየ ይህ ነው የሚባል እርምጃ አለመውሰዱ ስላሳሰበን ነው መግለጫውን ያወጣነው ያሉን የእናት ፓርቲ የብሄራዊ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ዳዊት ብርሃኑ ነግረውናል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከዳባርቅ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ሲመለሱ በታጣቂዎች የታገቱ 167 ተማሪዎች ጉዳይ ፓርቲዎቹ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የፀጥታ መዋቅሩ የንፁኃንን ደህንነት እየጠበቀ አይደለም የሚሉት አቶ ዳዊት መንግስት መዋቅሩን መፈተሽ አለበትም ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ ሃሳባቸውን የሰጡን የኢሃፓ ዋና ፀሃፊ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን እተፈፀመ ያለው እገታ የሃገረ መንስትቱ ስሪት የፈጠረው ችግር ነው ይላሉ፡፡
እዚህም እዚያም የተፈጠሩ ታጣቂዎች እገታን የገንዘብ ማግኛ መንገድ አድርገውታል በማለት ፓርቲቸው በጉዳዩ ዙሪያ ምን እየሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ሁሉንም ፓርቲዎች በአባልነት የያዘው የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ለሚፈፀሙ እገታዎች መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወስድና እልባት እንዲሰጥ እየተነጋገርኩ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ ባወጡት የጋራ መግለጫቸው ከ4 ዓመታት በፊት በ2012ዓ.ም ህዳር ወር ላይ በታጣቂዎች ታግተው ደብዛቸው የጠፋው የደምቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ጉዳይን በተመለከተ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ… https://shorturl.at/Koq9V
ምንታምር ፀጋው
ንጋቱ ረጋሣ
Comments