ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተናግሯል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ መሸጋገሩን ምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡
እንቅስቃሴው የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ መጣሉንም ጠቅሷል፡፡
የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ህግ እና ስርዓት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ እንቅስቃሴው በሃገር ደህንነት እና በህዝብ ሰላም ላይ የደቀነው አደጋ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ምክር ቤቱ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ የሰላም እና ህጋዊ መንገድን እንዲከተሉ መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ መቆየቱን መግለጫው አስረድቷል፡፡
የታጠቁ ቡድኖች እየፈፀሙት ባለዉ ጥቃት ምክንያት የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛልም ብሏል፡፡
የክልሉ መንግስትም ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ሁኔታውን በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ፣ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በኢፌድሪ ህገ መንግስት መሰረት እንዲደነግግ እና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ማቅረቡን የሚንስትሮች ምክር ቤት አስታውሷል፡፡
በመደበኛ የህግ ስርዓትን መሰረት አድርጎ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ተናግሯል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስራ ላይ ባልሆነበት ወቅት በመሆኑ ለእንደራሴዎች ቤት የሚቀርበው በ15 ቀናት ውስጥ ነው፡፡

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments