‘’በአማራ ክልል ነፍጥ አንስተው የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ ከተወሰኑት ጋር በሚስጢር ንግግር ከጀመርን ውለን አድረናል’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ከመንግሥት ጋር በተቃርኖ የቆሙ ሀይሎች ጋር ቀጣይነት ያለው ንግግር እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
ሰላም ለማምጣት ከታጣቂዎቹ ጋር የሚደረገው ንግግር ውጤት ላይ ያልደረሰው ‘’በአንድ ስም የሚጠሩ ብዙ ሀይሎች በመኖራቸው ነው’’ ብለዋል።
በተመሳሳይ ከ’’ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ንግግር እየተደረገ ነው’’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በተመሳሳይ ለውጤት ያልበቃው ‘’በአማራ ክልል እንዳሉት ታጣቂዎች በአንድ ስም የሚጠሩ ብዙ ሀይሎች ስላሉ ነው’’ ብለው አስረድተዋል።
‘’ባለፉት ሁለት ሶስት ወራት እስከ አምስት ጊዜ የደረሱ ወደ አላስፈላጊ መንገድ ሊወስዱ የሚችሉ ትንኮሳዎች ትግራይ ካሉ ሀይሎች በኩል ተደርጎብናል’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህ ግን ወደ ግጭት እንዳይወስደን፣ አያስፈልግም ብለን 10 ጊዜ ወይይት አድርገን ጉዳዩ መስመር እንዲይዝ አድርገናል ብለዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዲህ ብለው የተናገሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ከመንግሥት ሀላፊዎች እና ከፋይናንስ ዘርፍ ሰዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ሀገሪቱ ላሉባት የኢኮኖሚ ችግሮች ‘’የኮሶ መድሃኒት ነው’’ ብለዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያው በጣም ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ይህ ‘’እንኳን ደስ አላችሁ የሚያስብል ነው’’ ሲሉ አስረድተዋል።
በማሻሻየው ሌላው ቢቀር እንኳን ብዙ ችግር ያለበትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ማዳን ተችሏል፤ 4.9 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ማሻሻያው ለአንድ ዓመት ያህል መንገራገጭ ሊያመጣ እንደሚችል ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት የኑሮ ጫና ሊበረታባቸው የሚችል ዝቅተኛ ደምወዝተኞች እስከ 300 በመቶ ደመወዝ ይጨመራል፣ለገበሬው ማዳበሪያ ላይ እንዲሁም በነዳጅ ላይም ድጎማ ይደረጋል ብለዋል።
ሪፎርሙን ጠንክረን ሰርተን አንደምናሳካው እርግጠኛ ነኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርት በመያዝ፣ ዋጋ በመጨመር ችግር የሚፈጥሩት ለይ ህግ አስከባሪ አካላት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ እርምጃ ይወስዳሉ ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሳካ የአለም ባንክ ፣የአለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) የበላዮችን፣ የእንግሊዝ መንግስት እንዲሁም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድንን አመስግነዋል ።
ንጋቱ ሙሉ
Comments