top of page

ሐምሌ 25፣2016 - ‘’የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ድርሻ እጅ ማውጣት ብቻ እየሆነ ነው ወይ?’’ - የምክር ቤት አባል

‘’የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ድርሻ እጅ ማውጣት ብቻ እየሆነ ነው ወይ?’’ ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ጠየቁ፡፡


አበባው ደሳለው የተባሉ የምክር ቤት አባል ይህን ጥያቄ የጠየቁት ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የልማት ማህበር የተበደረችውን የ40 ቢሊዮን ብር ብድር እና የ80 ቢሊዮን ብር ወይም የአንድ የአሜሪካ ቢሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነቱን ለማጽደቅ ምክር ቤቱ በጠራው አስቸኳይ ስበሰባ ላይ ነው፡፡


ሰሞኑን ኢትዮጵያ ያደረገቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽያ እና እሱን ለመደገፍ ይረዳል ያለችውን ብድር ለማግኘት የወሰነችው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ መር እንዲሆን ማድረጉ በምክር ቤቱ አባላት የህጋዊት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡


የምክር ቤት አባሉ ‘’የገንዘብ እና ብሄራዊ ባንክ አስተዳደር የውጭ ምንዛሬ ልውውጥን በተመለከተ ምክር ቤቱ ዝርዝር ህግ እንደሚያወጣ ህጉ ያስረዳል ነገር ግን ከዚህ በፊትም በነበረው አሁንም እየሆነ ያለውም ህግ አስፈጻሚው ነው ህግ እያወጣ ያለው የህዝብ ተወካዮች ድርሻ ምንድነው ነው’’ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‘’ነገር ግን እኛ ህዝባችን አናሳትፍም፣ ምክር ቤቱ አይመክርበትም ይህም ከህጉ አንፃር እንዴት ይታያል?’’ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡


መሰል የኢኮኖሚ ማሻሽያዎች ሲደረጉ ህገ መንግስቱ በአንቀጽ 89 ንዕስ አንቀጽ 6 የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተመለከተ መንግስት በየደረጃው ህዝቡን ማሳተፍ እንዳለበት መደንገጉንም ጠቅሰዋል፡፡


ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ‘’የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽያው እድገት የተደረገ ሳይሆን ህዝቡ የተወያበት ምክር ቤቱም የመከረበት ጉዳይ ነው’’ ሲሉ ተከራክረዋል፡፡


የምክር ቤት አባሉ አክለውም ‘’ከራሳችን ለሚመጡ ችግሮች መፍትኤዎችም የራሳችን እንዲሆኑ በርካታ ወይይቶች እና ድርድሮች እንደተደረጉ እንደ ዜጋም እንደ ምክር ቤት አባልም እናውቃለን በተደረሰበት ማሻሽያም ለሀገር ይጠቅማል የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ የመጣ’’ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው በሰጡት ምላሸ ‘’የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሽያው የድንገት ውሳኔ ሳይሆን ባለፉት አምስት ስድስት አመታት ሲተገበር የነበረ ነው’’ ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑ በማህበረሰቡ ላይ ለሚደርሰው ተጽኖ ዝግጅት ተደርጓል ወይ? ለምስን በድንገት መወሰን አስፈለገ ተብለው ከምክር ቤት አባል የተጠየቁት አህመድ ሽዴ ለሚደርሰው ተጽኖ መንግስት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


በመጀመሪያ ወራቶች ወይምን አመታት ጫና እንደሚመጣ ይታወቃል፡፡


በዘላቂነት ግን የዋጋ ንረትን ለመፍታት ከዚህ ውጪ አማራጭ ያለንም ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Kommentare


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page