ሐምሌ 25፣2016 - በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ እንደ ወባ እና ኮሌራ ያሉ የህብረተሰብ የጤና ችግሮች ጨምረዋል ተባለ
- sheger1021fm
- Aug 1, 2024
- 1 min read
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ድርቅና መፈናቀል ተከትሎ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ እንደ ወባ እና ኮሌራ ያሉ የህብረተሰብ የጤና ችግሮች ጨምረዋል ተባለ።
በሀገሪቱ 69 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ከመልካ ምድራዊ አቀማመጥ በተለይ ለወባ ተጋላጭ መሆኑ ተነግሯል።
የጤና ሚኒስቴር ወቅታዊ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች ባላቸው ወባ ኮሌራ እና ኩፍኝ በሽታዎችን ላይ በመድሃኒት እና ህክምና ስራው ላይ የከወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።
በተለይ ወባ ከዚህ ቀደም በተከወኑ የመከላከል ስራዎች ቀንሶ የነበረ ቢሆንም አሁንም ግን በአስር ክልሎች በሚገኙ 222 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ስርጭት እየታየበት ነው ተብሏል።

ከክልሎች ጋር በመሆን አስቸኳይ ማስተባበሪያ ኮሚቴ ተቋቁሞ የመድኃኒት የኬሚካልና የአጎበር ስርጭት ላይ እየተሰራ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ(ዶ/ር) ተናግረዋል።
ከመጋቢት ጀምሮ የነበረው የተዛባ የዝናብ ስርጭትን ተከትሎ ከዚህ ቀደምም የወባ ስጋት በነበረባቸዉ አካባቢዎች የወባ በሽታ ስርጭቱን ተስፋፍቷል ተብሏል።
ከመጪው መስከረም እስከ ታህሳስ ያሉት ጊዜያትም የወባ በሽታ የሚስፋፋበት በመሆኑ ከወዲሁ የተለያዩ የመከላከልና መቆጣጠር ስራዎች መከወናቸውን ዶክተር መቅደስ ተናግረዋል።
ከነዚህም ውስጥ ከክልሎች በተገኘ መረጃ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ህክምና ተሰጥቷል፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ መድሃኒት፤ ሰባት ሚሊዮን የመመርመርያ ኪት ወባ ለተከሰተባቸው አካባቢዎች መሰራጨቱ የተነገረ ሲሆን ይህም በሽታው ካለው ስጋት አንጻር ከተያዘው እቅድ ተጨምሮ የተከፋፈለ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል በተለያዩ ክልሎች በአንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ወረዳዎች በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የነበረውን ኮሌራ በአንድ መቶ ዘጠኝ ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

ቀሪ 43 ወረዳዎች ላይ ግን አሁንም የኮሌራ ወረርሽኝ አለ ብለዋል።
የኩፍኝ በሽታን በተመለከተም በሽታው በታየባቸው ክልሎች ላሉ እንዲሁም በመደበኛ ዘመቻ ምንም ክትባል ላልወሰዱ 600 ህፃናት ክትባት መሰጠቱና ተጨማሪ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ህጻናት ክትባቱ እየተሰጣቸው እንደሚገኙ ሰምተናል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ…
ምህረት ስዩም
Comments