የኩላሊት እጥበት ህክምና (ዲያለሲስ) ለማድረግ በግል ሆስፒታሎች በሳምንት እስከ 15,000 ብር እየተጠየቁ መሆኑን ታማሚዎቹ ተናገሩ።
ዋጋው በዚህ ከቀጠለ ከሰሞኑ እየታየ ያለው የዶላር የምንዛሪ ዋጋ ህክምናውንም መድሃኒቱንም ይበልጥ ሊያስወድድብን ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው።
250 የኩላሊት ታካሚዎችን በአባልነት የያዘው ተስፋ የኩላሊት ታካሚዎች ማህበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለህክምና እና ለመድሃኒቶች ግዢ የሚጠየቀው ገንዘብ ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብሏል።
ህሙማኑን ለማገዝ ብቋቋምም ደጋፊ በማጣት መርዳት አልቻልኩም፣ ህሙማኑም አደጋ ላይ ናቸው የሚለው ማህበሩ፤ በቀን 35 ሳንቲም በወር ሲሰላ 10 ብር እርዱን ሲል ሲሉ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መስፍን አስረስ ጥሪ አቅርበዋል።
ማህበሩ የ10 ብር ፕሮጀክት ሲል የሰየመውን መርሃ ግብርም ትላንት ይፋ አድርጓል።ከልገሳው የሚገኘው ገንዘብ ለኩላሊት ታካሚዎች ህክምናና ለኩላሊት ህክምና ማዕከል ግንባታ የሚውል ነውም ተብሏል፡፡
የኩላሊት ሆክምና ውድ በመሆኑ ብዙዎች ለመታከም ያፈሩትን ሃብት አሟጥጠዋል፤ ያልቻሉ ደግሞ እጃቸውን ለልመና ሲዘረጉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል::
ከ6 ዓመታት በፊት በ5 የኩላሊት ህሙማን የተመሰረተው ማህበሩ 250 ከደረሱት አባላቱ 50ውን በህመሙ ምክንያት በሞት ማጣቱን ነግሮናል።
ለህሙማን ለመድረስ መለገስ የምትፈልጉ በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሃገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እጃችሁን ዘርጉልኝ ሲል የባንክ የሂሳብ ቁጥሮችንም ይፋ አድርጓል።
ለዚህም 3136 አጭር ቁጥር፤በንግድ ባንክ፤ 1000357877408 እንዲሁም በዳሽን ባንክ 5022881951011 የሂሳብ ቁጥሮች ተከፍተዋል፡፡
Comments