የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪ ቀለብ የሚመደብላቸው ብር ስለማይበቃቸው ካላቸው የተማሪ ቁጥር ጨምረው እያቀረቡ ነው ሲል የትምርት ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
በተደረገ ማጣራትም ዩኒቨርሲቲዎቹ የማያስተምሯቸው 251,000 ተማሪዎችን ቁጥር ጨምረው ሪፖርት አድርገዋል ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ በቀን ለአንድ ተማሪ የሚመደብላቸው 22 ብር ስለማይበቃቸው የውሸት ቁጥር ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ይህንን በመገንዘብ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውና የሚመግቡት ተማሪዎች ብዛት ትክክለኛነት ለማወቅ ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲልኩ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች እንመግባቸዋለን ብለው ለገንዝብ ሚኒስቴር ካስገቡት የተማሪዎች ቁጥር እና ለትምህርት ሚኒስቴር ከተላከው ጋር ሲተያይ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ያለው ሆኖ እየተገኘ ነው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር) አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም አምና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለገንዘብ ሚኒስቴር ያስገቡት የተማሪዎች ቀጥር ለትምህርት ሚኒስቴር ከላኩት ጋር ሲተያይ የ250,000 ልዩነት ጭማሪ አለው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ ለዚህ የውሸት ሪፖርት ያበቃቸውም ለሚመደብላቸው የቀን የተማሪ የቀለብ በጀት ከጊዜው ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ እንደሆነም ፕ/ር ብርሀኑ ተናግረዋል፡፡
ይህንን የተበላሸ አሰራር ከዚህ በኋላ መቀጠል የለበትም ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ በጀትም፣ ሌላውንም መመስተት ያለበት በትክክለኛ መረጃ መሰረት መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን ያዘጋጀውን በምህረት ስዩም
Comments