top of page

ሐምሌ 23፣2016 - ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ የሚቀርቡ የምግብ ፍጆታዎች አቅርቦት አሁንም የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም እንዳለ ተነገረ

በአዲስ አበባ ከተማ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ የሚቀርቡ የምግብ ፍጆታዎች አቅርቦት ካለፈው ዓመት የተሻለ ቢሆንም አሁንም የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም እንዳለ ተነገረ፡፡


የሸማች ህብረት ስራ ማህበራቱ በሚያቀርቧቸው ፍጆታዎች ላይ የገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ከተማ አስተዳደሩ ከ1.4 ቢሊየን ብር በላይ ብድር እንዳመቻቸላቸው የተናገሩት የህብረት ስራ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር ጥላሁን ጌታቸው ናቸው፡፡


ከ2.9 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የግብርና ምርት ለከተማዋ ነዋሪ መቅረቡን የተናገሩት አቶ ጥላሁን በመንግስት ድጎማ የተደረገባቸው ምርቶች ደግሞ 3.1 ቢሊየን ብር ገደማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


በዚህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በማህበራቱ የቀረበው የምግብ ፍጆታ እና ሸቀጥ ከፍ ያለ ቢሆንም አሁንም ግን የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም እንዳለ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡


በየጊዜው የሚታይ የዋጋ ጭማሪ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦት በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ ውስንነትን ይፈጥሩብናል የተባለ ሲሆን ህገ-ወጥ ደላሎችም መኖራቸው በበጀት አመቱ ያጋጠሙን ችግሮች ነበሩ ብለውናል የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክትር ጥላሁን ጌታቸው፡፡


በከተማዋ የሚታየውን የሸቀጦች ዋጋ መናር ለማረጋጋት ማህበራቱ ቀጥታ ከአምራቾች ለማህበረሰቡ ከሚያቀርቡባቸው መንገድ አንዱ የቅዳሜ እበና የእሁድ ገበያዎች አንዱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተደራሽነትን ማስፋት ቢቻልም ይዘውት የሚቀርቡት ምርት ውስን በመሆኑ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን ምርት በተሟላ መልኩ እያገኘ አለመሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ተናግሮ ነበር፡፡


ችግሩን ለመፍታትም በሁሉም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ይዘውት የሚወጡትን ምርት በተመለከተ ስታንዳርድ ለማውጣት እየተሰራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ምን ዓይነት ምርት መያዝ እንዳለባቸው እና ምን ዓይነት የጥራት ደረጃዎችን ማሟላት እንዳለባቸው የሚያደርግ መሆኑ ተነግለታል፡፡


መስፈርቱም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፤ ይህም የምርት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ተብሏል፡፡


በ2016 በጀት ዓመት በየቅዳሜና እሁድ ገበያ በቀረቡ ምርቶች ግብይት ብቻ ከ650 ሚሊየን ብር በላይ መንቀሳቀሱን ከኮሚሽኑ ሰምተናል፡፡


ፋሲካ ሙሉወርቅ



Comments


bottom of page