top of page

ሐምሌ 22፣2016 - የውጭ ምንዛሪ ግብይት  በገበያው አማካይነት እንዲሆን ተወሰነ። 

በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል፣ የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።


በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠንም ለማስተካከል ይረዳል፣ ሌሎችም ጥቅሞች አሉት ሲል መንግስት ተናግሯል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የፖሊሲ መግለጫ በሚል በዛሬው እለት መንግስት ባወጣው መግለጫ አራት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስረድቷል።


ከእነዚህ መካከልም የውጪ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲተመን የሚለው ይገኝበታል።


በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ሌላኛው ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የማሻሻያ ርምጃ የገንዘብ ፖሊሲ ማህቀፉን ማዘመን ነው።


የ3 ዓመት የብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ንረት መኖሩን ማረጋገጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ባንኩ ከንግድ ባንኮች ጋር በሚያደርገው የንግድ ግብይት በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ቅድሚያ ይሰጣል።


ሌላው ማሻሻያ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ ነው። የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያችን የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን እንዲቀንሱ ያደርጋል።


የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያው ዋና ትኩረቱ የመንግሥት ገቢን ማሳደግ፤ የመንግሥት ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የመንግሥት ብድር አስተዳደር ውጤታማና አዛላቂ እንዲሆን ማረጋገጥ ናቸው።


እነዚህ እርምጃዎች የበጀት አስተዳደር ውጤታማነትን እና የመንግሥት ዕዳ ተጋላጭነትን ያሻሽላሉ ተብሎ ታምኖበታል።


ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስታዳደር ማሻሻያ ነው።


ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከተለያዩ አበዳሪዎቻችን ጋር በመነጋገር ከፍተኛ የዕዳ ማሻሻያ ርምጃዎችን ለመውሰድ እየተሠራ ነው ያለው መግለጫው በሌላ በኩል ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በተለይም ከዓለም ባንክ፣ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ባንኮች እና ከሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል ብሏል።


በዚህም መሠረት ሀገሪቱ በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትግበራ መሠረት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ቢልዮን ዶላር ታገኛለች ብሏል።


ይሄም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እየጠበቁ ካሉ ከሌሎች የልማት አጋሮቻችን ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍን ለማሰባሰብም ያግዛል ሲል አስረድቷል።


የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ቁልፍ ዓላማዎች እና ግቦች፡-


(1) የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ከፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፣


(2) የገንዘብ ፖሊሲ ማህቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፣


(3) የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፤


(4) የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር፣ እና


(5) የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፤ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።


ንጋቱ ሙሉ


コメント


bottom of page