ሐምሌ 22፣ 2016 ብሔራዊ ባንክ ከአጋሮች 10.7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ተናገረ።
- sheger1021fm
- Jul 29, 2024
- 1 min read
ሐምሌ 22፣ 2016
ብሔራዊ ባንክ ከአጋሮች 10.7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ተናገረ።
የሽግግር ወቅት ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎችን ለመቀነስ የሚረዳ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች ተገኝቷል " ሲሉ የብሔራዊ ባንኩ ዋና ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ተናግረዋል።
የገንዘብ ድጋፉ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ፣ ከዓለም ባንክ እና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ሪፎርሙን የሚመለከተውን እንደሚጨምር ገዢ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከወዳጅ ሀገሮች በማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ (central bank deposit) እና በከረንሲ ልውውጥ (currency swap) መልክ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ተብሏል።
ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እና ከሌሎች ባለብዙ ወገኖች (multilateral) ፕሮጀክትን አስመልክቶ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውንና በሃደት ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ይፋ የሚደረገውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አያካትትም ሲሉ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ጠቅሰዋል።
ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ፣የዓለም ባንክ እና ወዳጅ ሀገራት የተገኘው ሀብት የመንግሥትን የሪፎርም ሥራዎች ጥንካሬ ያገናዘበና በአፍሪካ አህጉር ትልቁ ከሚባሉት የገንዘብ ድጋፎች መሆኑንም ገዢው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሷል።
በትናንትናው ዕለት መንግሥት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ የስጠውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው ዕለት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን አስረድቷል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውለው ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽል ታምኖበታል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comments