top of page

ሐምሌ 2፣ 2016 - ወጣቶች ሀገራዊ ምክክሩን ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ተፅዕኖ እንዲጠብቁ ተጠየቁ

  • sheger1021fm
  • Jul 9, 2024
  • 1 min read

ወጣቶች ሀገራዊ ምክክሩን ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ተፅዕኖ እንዲጠብቁ ተጠየቁ፡፡


በሀገሪቱ 70 በመቶ የሚሆነውን የህዝብ ቁጥር የሚሸፍነው ወጣቱ ሀገራዊ ምክክሩ ከየትኛውም ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡


ኮሚሽነሩ ‘’በሀገሪቱ ግጭት ግጭትን እየወለደ ሞትና መገዳደል መፍትሄ እያመጣ እንዳልሆነ አይተናል ለዚህም የንግግሩን መንገድ መሞከር አስፈላጊ ነው’’ ብለዋል፡፡


ምክክሩ እንዲሳካ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወጣቱ ደግሞ በምክክሩ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል፡፡


ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ከ10,000 በላይ ግጭቶች ተፈጥረዋል ያሉት ኮሚሽነር ዶ/ር አምባዬ ይህም በምን ዓይነት መንገድ ላይ እንዳለን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡


ለዚህም በተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ላይ ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ኮሚሽኑ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡

በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ወጣቱ ለመነጋገር እንዲዘጋጅ የጠየቁት ዶ/ር አምባዬ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አላማው እንዳይጠለፍም ከመንግስት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከኮሚሽነሮች ፍላጎት እንዲጠብቁት ጠይቀዋል፡፡


የኢትዮጵያ ፖለቲካ መደማመጥ የሌለበት፣ ብዙ ተናጋሪዎች የሞሉበት መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ አሁን ካለንበት አለመግባባት መደማመጥ ስንችል ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ዓይን የምታይ ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ወጣቱ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ድርሻው ምን እንደሆነ ራሱን መጠየቅ አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ በአገሩ ጉዳይ ዳር ቆሞ ተመልካች ሳይሆን ባለቤት እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡


ሌሎች ሀገራት ወጣቱ ካለባቸው ጥቁር ጠባሳ እንዲወጡ ከፍተኛ ድርሻ ተወጥተዋል ያሉት ኮሚሽነር አምባዬ እኛ ግን የቀደመ ታሪካችንን መጋፈጥ ፈርተናል ብለዋል፡፡፡


የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመላው ሀገሪቱ ከተወጣጡ 200 ወጣቶች ጋር ውይይት ዛሬ እያደረገ ነው፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page