በዓመቱ ወደ ተለያዩ አገራት ከተላከ 298 ሺህ 500 ቶን ቡና 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል ተብሏል።
ዘንድሮ ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላከ ቡና ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷ ተነግሯል።
ገቢው ከዚህ ቀደም ተገኝቶ የማያውቅ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ነግረውናል።
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ገቢ ወደ ውጪ ከተላከ ቡና የተገኘው ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የዘንድሮው ግን ከዚያም የበለጠ ሆኗል ብለዋል፡፡
ቀይ ባህር ላይ በሰኔ የመጨረሻ ሳምንት በተፈጠረ ችግር ቡና መላኩ ለአንድ ሳምንት ባይቋረጥ ኖሮ፤ ገቢው ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር አዱኛ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከፍተኛ ገቢ ከቡና ያገኘችው ግብይቱ የተለያዩ ፈተናዎች እያሉበት ነውም ብለዋል ዶክተር አዱኛ።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት የአውሮፓ አገራት ቀዳሚዎቹ እንደነበሩ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘንድሮ ግን የእስያ አገራት ደረጃውን ተረክበዋል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት የቡና ግብይትን በተመለከተ አዲስ ህግ ማውጣቱ ይታወሳል።
ህጉ በቡና ማምረት ሂደት ጫካ የሚመነጠር ከሆነ በህብረቱ አባል አገራት አገሮች እንዳይሸጥ የሚከለክል ነው።
ዕድሜያቸው ለስራ ያልደረሰ ህጻናት በምርት ሂደቱ ከተሳተፉም ከሰብአዊ መብት ጥሰት የሚቆጠር ስለሆነ በዚህ መልክ ለገበያ የሚቀርብን ቡና አልገዛም ብሏል።
ይሄ የህብረቱ ህግ በኢትዮጵያ የቡና ግብይት ላይ ያሳደረው ጫና ካለ? በሚል ዶክተር አዱኛ ደበላን ጠይቀናቸዋል።
የቡና ግብይት ከምርት ገበያ ውጪ ባሉ አማራጮች እንዲካሄድ መወሰኑም ይታወሳል።
የአማራጮቹ መስፋት ገቢው እንዲያደግ ያደረገ አንዱ ምክንያት ስለመሆኑ ተጠቅሷል።
ቡና ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል።
ንጋቱ ረጋሣ
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments