በአዲስ አበባ ህገ ወጥ ናችሁ በተባሉ 50,000 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡
በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው እየሰሩ ያሉ ከ400,000 በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውን የሚናገረው የከተማዋ ንግድ ቢሮ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች ህገ ወጥ ሆነው ተገኝተዋል ብሏል፡፡
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሰውነት አየለ በዓመቱ ባደረግነው የቁጥጥር ስራ 50,100 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል ገሚሱ ላይ የማሸግ እርምጃ ሲወሰድባቸው ሌሎቹ ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸው ታግዷል፣ የተቀሩት በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የነዋሪውን የኑሮ ጫና ያቃልላሉ ተብለው በከተማዋ ባሉ መግቢያና መውጫ በሮች በተከፈቱት የገበያ ማዕከላት የግብርና ምርቶች ከገበያው ዋጋ ከ15-20 በመቶ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ምርቶችን እየሸጡ መሆኑን ጤፍን ለአብነት በመጥቀስ ነግረውናል፡፡
በገበያው ላይ ከ16,000 17,000 ብር እየተሸጠ ያለው ጤፍ በእነዚህ ገበያዎች ግን ከ12,000 ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ምንም እንኳን የገበያ ማዕከላቱ በሚሰጡት አገልግሎት ተመራጭ እየሆኑ ቢመጡም ያሉበት ቦታ ከዋናው መንገድ ገባ ብለው መገኘታቸው፣ መውጫ መግቢያቸው ከክረምቱ ጫቃ ጋር አላራምድ የሚል መሆኑ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎችም መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው መሆናቸውንም ጠቁመውናል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በ2017 ዓ.ም በ1.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የገበያ ማዕከላትን እንደሚገነባና 190 የደረሱትን የእሁድ ገበያዎች በጥራትም እንደሚጨምር ከሃላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ… https://tinyurl.com/5jpru9jp
ምንታምር ጸጋው
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments