ሐምሌ 19፣ 2016 - ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ህፃናት በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጥናት አሳየ
- sheger1021fm
- Jul 26, 2024
- 1 min read
ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ህፃናት የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች ስለማያገኙ በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጥናት አሳየ።
ወላጆቻቸው ጥፋት አጥፍተው ተፈርዶባቸው ወደ ማረሚያ ቤት አብረው የሚገቡ ህጻናት፤ መሰረታዊ የሚባሉ መብቶቻቸውን እያገኙ እንዳልሆነ ተነግሯል።
ይህንን ባደረኩት ጥናት አረጋግጫለሁ ያለው ሴንተር ፎር ጀስቲስ(Center For Justice) የተሰኘ ተቋም ነው።
ህፃናቱ በተለይም ትምህርት በማግኘት በኩል በብዙ የሀገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ክፍተቶች አሉ ብሏል ተቋሙ።
ጥናቱን ያጠናው ሴንተር ፎር ጀስቲስ ዳይሬክተር ኩምሳ ጉተታ፤ ካለፉት 6 ዓመታት ወዲህ በማረሚያ ቤቶቹ ዙሪያ የተሻሻሉ አሰራሮች ቢኖሩም በህጻናት አያያዝ ላይ ግን ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይናገራሉ፡፡
ለህፃናቱ ተብሎ የሚያዝ የተለየ በጀት አለመኖሩና እንደ አንድ ታራሚ መቆጠራቸው ሌላው ችግር ነው ተብሏል።
እንዳንድ እናቶች ሁለት ሶስት ህፃናትን ይዘው ማረሚያ እንደሚገቡ የሚጠቅሱት አቶ ኩምሳ ለህጻናቱ የምግብ፣ የአልባሳት ችግር በዚህ ጊዜ ይከፋል ብለውናል፡፡

በጥናቱ ተገኝተዋል የተባሉ ችግሮችን በተመለከተ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከሚሽንን አነጋግረናል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ፤ በጥናቱ የተጠቀሱት ችግሮች በማረሚያ ቤቶች እንዳሉ አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህም በኛ አቅም የሚሰሩትን ሆነ ከሌሎች እገዛ የሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ እየሰራን እንገኛለን ብለውናል፡፡
ለታራሚዎች የጤና አገልግሎት ከመስጠት አንጻርም ተጨማሪ ክፍተት በማረሚያ ቤቶቹ እንዳለ ተነግሯል።
የጤና አገልግሎት ከመስጠት አንጻር በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ከክልሎቹ በብዙ የተሻሉ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
በማረሚያ ቤቶች የሚታዩ እነዚህ ችግሮች በህጻናቱ ጤንነትና እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድሩባቸዋልም ሲል ጥናቱ ተናግሯል።
በጥናቱ ለተገኑ ግኝቶችና ችግሮች እንደመፍትሄ የቀረቡ ሀሳቦችም ተዘርዝረዋል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comentarios