top of page

ሐምሌ 19፣ 2016 - ከአማራና ትግራይ ክልሎች ውጪ ክልሎች እስከ መስከረም መጨረሻ የአጀንዳ ማሰባሰብ እንደሚያጠናቅቅ የሀገራዊ ምክክር ተናገረ

ከአማራና ትግራይ ክልሎች ውጪ ባሉት 10 ክልሎች እስለ መስከረም መጨረሻ ድረስ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚያጠናቅቅ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተናገረ፡፡

 

ኮሚሽኑ ይህን የተናገረው ዛሬ በአዳማ ከተማ ከተለያዩ ክልሎች ከተወጣጡ አካል ጉዳተኞች ጋር እያካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

 

ውይይቱ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በአገራዊ ምክክሩ ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

 

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጎጆ በኢትዮጵያ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ቀዳሚ ተጎጂው ሮጦ ማምለጥ የማይችለው አካል ጉዳተኛው ነው ተብሏል፡፡

 

አሁን ካለንበት ግጭት መውጫው መንገድ ደግሞ ምክክር ነው ያሉ ሲሆን እየተካሄደ በሚገኘው የአገራዊ ምክክር ላይ መሳተፍ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የ50 እና የ60 ዓመት ታሪካችን ችግሮችን በጦርነት መፍታት እንደማይቻል ነግሮናል ያሉ ሲሆን በአገሪቱ በሚፈጠረው ግጭቶችም ቀዳሚ ተጎጂዎች የአካል ጉዳተኞች ናቸው ብለዋል፡፡

 

ግጭት ወይም ጦርነት ዛሬ አንዱን ነገ ደግሞ ሌላውን አሸናፊ ያደርጋል እንጂ ቋሚ መፍትሄ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

 

ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን ግን ምክክር ብቻ ነው ብለዋል፡፡

 

ይህንንም ተረድቶ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከሁሉም ተቋማት አስቀድሞ አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ የቀረበ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ በ10 ክልሎች የአጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደሚያጠናቅቅ የተናገረ ሲሆን በትግራይና በአማራ ክልል ደግሞ ሁኔታዎች ሲመቻቹ በማንኛውም ጊዜ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እንደሚጀመር አስረድተዋል፡፡

 

የዛሬው መድረክ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና በኢትዮጵያ  የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

 

ያሬድ እንዳሻው

Comments


bottom of page