በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ አንዳንድ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የክፍል እጥረት ስላጋጠማቸው የፈረቃ ትምህርት ለመጀመር እየተገደዱ ነው፡፡
ይህ የተባለው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከሁሉም የከተማው የትምህርት ቤት ኃላፊዎችና አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው፡፡
የተለያዩ የክፍለ ከተማ የትምህርት ቢሮ አመራሮች እንደተናገሩት አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ የተማሪ ብዛትና ያለው ክፍል ባለመጣጣሙ በ2017 የትምህርት ዘመን የክፍል ማነስ የገጠማቸው ትምህርት ቤቶች የፈረቃ ትምህርት ለመጀመረ እንደ ወሰኑ ሰምተናል፡፡
በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች በአንድ ክፍል እስከ 90 ተማሪዎች እንደሚማሩ ሲነገር ሰምተናል።
ይህም ትምህርት ጥራት ላይ ችግር እንዳያመጣ ስጋት አለን ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአካቶ ትምህርት ለመተግበር በሙያው የሰለጠነ መምህር እጥረት፣ ለአይነ ስውራን ተማሪዎች የብሬል መፅሀፍ አልደረሰም የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተሳታፊዎቹ ለከተማው ትምህርት ቢሮ አመራሮች ቀርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ታጋይቱ አባቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የብሬል መፅሀፍ ህትመት በዚህ ዓመት እንደሚደረግና ለተማሪዎች ይሰጣል ብለዋል፡፡
ነገር ግን ትምህርት ቤቶች የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ለመመዝገብ ዳተኝነት ይታይባቸዋል ይህንን ሊያስተካክሉ ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው እንደ ከተማ በእንግሊዘኛ ትምህርት እና በሂሳብ ትምህርት ውጤቶች ዝቅተኝነት መሆኑን በመጥቀስ የተማሪዎች አቅም ለማሻሻል ያሰበ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚተገበር ስራዎች እየተከወነ ነው ብለዋል።
የትምህርት ጥራት ለማምጣት ካስፈለገ የተማሪዎች ስነ ምግባር ማስተካከልና መምህራን የስነ ምግባር ክፍተት ሲያሳዩ እንዲያርሙ ሊደረግ ይገባል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በዚህ አመት በ6 ተኛ እና 8 ተኛ ክፍል ፈተና ላይ የማታ ተማሪዎች ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው የተባለ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ይህንን ችግር ከመምህራኑ ጋር በመነጋገር ለውጥ እንዲመጣ ሊሰሩ ይገባል መባሉን ሰምተናል፡፡
ከክፍል እጥረትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይደረግባቸው የስብሰባው ማጠቃለያ በዝግ በመደረጉ ሸገር ምላሹን መስማት አልቻለም፡፡
በረከት አካሉ
Comments