በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ66,000,000 ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ተናገረ።
ለመንግስት ካዝና የገባው 66,000,000 ብር ህግ ተላልፈው ከተገኙ ከ6,000 በላይ ህገ-ወጥ ተግባራት ከፈፀሙ ሰዎች ላይ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ይህንን የሰማው በ2017 በጀት ዓመት አብረውት ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።
በበጀት ዓመቱ የተገኘው የገንዘብ መጠንም ከጨረታ እና ከቅጣት የተገኘ እንደሆነ የተናገሩት የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ህገወጥ የመሬት ወረራ፣ ህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ፣ ህገወጥ የእንስሳት እርድ እና ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተገኙ ከስድስት ሺህ በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ ያለውን ህገወጥ ድርጊቶች ሲከታተል የቆየው፤ ከ23 የመንግስት ባለድርሻዎች ጋር እንደነበር የተናገሩተ ሻለቃ ዘሪሁን በመጭው በጀት ዓመት ከ38 የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ሚዲያዎች ጋር ስራዎችን ሊከውኑ እንዳቀዱ ሲናገሩ ሰምተናል።

በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመጭው በጀት ዓመት አብሬ እሰራለሁ ካላቸው ተቋማት ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰሩ ያሉ የአረንጓዴ ልማት እና መዝናኛ ስፍራዎች ላይ በህገ-ወጥ መንገድ ደረቅ እና ፍሻሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ደንብ የተላለፉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን እየቀጣ መሆኑን ሲነገር ሰምተናል፡፡
በኮሊደር ልማቱ የተሰሩ አረንጓዴ ስፍራዎችን በተሸከርካሪ መግጨትም ይሁን በአግባቡ አለመጠቀም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚቀጣ መሆኑ የተናገሩት የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ ይህንን እና ሌሎች ስፍራዎች ላይ የተከለከለ ድርጊት የፈፀመን ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከትንሹ 2,000 ብር እስከ 100,000 ብር እንደሚቀጡ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በ2016 በጀት አመት የደንብ መተላለፎችን ከማስከበር በተጨማሪ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መሰራቱ የተነገረ ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን እወቁልኝ ብሏል።
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comentarios