ሐምሌ 17፣ 2016 - ባለው ግጭት ምክንያት የተበዳዮችን ቅሬታ መሰብሰብ እንዳልቻለ የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ
- sheger1021fm
- Jul 24, 2024
- 1 min read
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለው ግጭት ምክንያት የተበዳዮችን ቅሬታ መሰብሰብ እንዳልቻለ የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ፡፡
በዚህም ምክንያት በተጠናቀቀው ዓመት ካሰብኩት ውስጥ ያሳካሁት 53 በመቶውን ብቻ ነው ብሏል፡፡
የአስተዳደር በደል ደረሰብን እምባችን ይታበስልን የሚሉ አቤት ባዮች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ እምባ ጠባቂ ተቋም በማምራት አቤቱታቸውን ያሰማሉ፡፡
ተቋሙም በፍርድ ከተያዙ ጉዳዮች፣ የሃገርን ደህንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉና የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ውጭ ያሉ ሁሉንም አይነት ጉዳዮችን ተቀብሎ በመመርመር ውሳኔ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2016 የበጀት ዓመት ከ44 ሺህ 912 አቤቱታ አቅራቢዎች የተቀበለው አቤቱታ 1,972 መሆኑን ተናግሯል፡፡

ዓመቱ ሲጀመር 3ሺ 720 የአቤቱታ መዝገቦች ለመቀበል ዝግጅት ቢያደርግም፤ በዓመቱ መጨረሻ የተቀመጠው 1,972 አቤቱታዎችን ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ካቀድኩት ውስጥ ማሳካት የቻልኩት 53 በመቶውን ብቻ ነው ብሏል፡፡
ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሰው በየአካባቢው ያለው ግጭት ተንቀሳቅሶም ሆነ በስልክ አቤቱታዎችን ለመቀበል መቸገራቸውን በኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተወካይ እምባ ጠባቂ የሆኑት አቶ ደነቀ ሻንቆ ነግረውናል፡፡
በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አቤቱታዎች የሚቀርቡበት የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የፀጥታ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ተገልጋዮች አቤቱታቸውን በአካል መጥተው ማቅረብ በመቸገራቸው የአቤቱታው ቁጥር እንዲያስ ምክንያት እንደሆነም ሃላፊው ያስረዳሉ፡፡
ከቀረቡ አቤቱታዎች ውስጥ 39 በመቶዎቹ ጉዳዮች እኛን የማይመለከቱ ማለትም በፍርድ ቤት የታዩና የወንጀል ጉዳዮች አቤቱታዎች በመሆናቸው ተገቢው የህግ ምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸው ተሸኝተዋል የሚሉት ሃላፊው፤ 1081 መዝገቦች ምርመራ ተደርጎባቸው ከእነዚህ ውስጥ 875 መዝገቦች መፍትሄ አግንተዋል፤ ቀሪ 206 መዝገቦች በምርመራ ሂደት ላይ ናቸው፤ በቀጣዩ ዓመትም እልባት ያገኛሉ ብለዋል፡፡
አቤቱታውን ተቀብለን ቀጣዩን የምርመራ ስራ ተንቀሳቅሰን መስራት ስላልቻልን በአማራ ክልል የገጠር ቀበሌዎች፣ በምዕራብ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ስራዎችን መስራት አልቻልንም ይላሉ፡፡
በዓመቱ ከቀረቡ አቤቱታዎች በአሰሪዎች የሚደርስ በደል ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ የመሬት ይዞታ ቅሬታ ሁለተኛው ነው፣በአገልግሎት ያለመርካት በሶስተኛነት ይጠቀሳል፡፡
ባለፈው 2015ዓ.ም ተቋሙ በመዝገብ የተደራጁ 4,712 ቅሬታዎችን የተቀበለ ቢሆንም በ2016 ዓ.ም የተሰበሰበው ግን በ2 ሺህ 740 ቀንሶ 1ሺህ 972 መሆኑን ከሃላፊው ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments