top of page

ሐምሌ 17፣ 2016 -  በጎፋ ዞን የደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ በመሬት እና ውሃ ጥበቃ ስራ በአግባቡ ባለመከወኑ ያጋጠመ እንደሆነ ተነገረ 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ በመሬት እና ውሃ ጥበቃ ስራ በአግባቡ ባለመከወኑ ያጋጠመ እንደሆነ ተነገረ፡፡

 

የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከፍተኛ የመሬት ናዳ እና መንሸራተት የሚያስከትል መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዚክስ የስፔስ ሳይንስ አስትሮኖሚ ተቋም ሀላፊ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ አስታውሰዋል፡፡

 

ይሁንና በደቡብ ኢትዮጵያ በክረምት ወቅት እያሰለሰ የሚያጋጥመው የአሁኑን ዓይነት የመሬት መንሸራተት ከአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ማነስ ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ፡፡

 

መታረስ የሌለባቸው ተራራማ ቦታዎች ለእርሻ ስራ ሲውሉ እና ደን ሲመናመን እንዲሁም የከርሰ ምድር የውሃ ቋቶች ባዶ ሲሆኑ መሰል የመሬት ናዳ እንደሚያጋጥም ፕሮፌሰር አታላይ ጠቅሰዋል፡፡

 

የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በአግባቡ ሳይከወን ሲቀር በዝናብ ጊዜ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር የመሰረግ እድሉ እየቀነሰ ሲመጣ የምድር ውስጥ  የተፈጥሮ የውሃ በርሜሎችም ባዶ ይሆናሉ ብለዋል ሀላፊው፡፡


በዚህም ምክንያት የመሬቱ የመንሸራተት እድሉ ከፍ እያለ እንደሚመጣ ጠቅሰዋል፡፡

በጎፋ ዞን ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት ከ229 በላይ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በርካቶችም ጉዳት ደርሶባቸው በጤና ተቋም እንደሚገኙ ሰምተናል፡፡

 

በአካባቢው በናዳው የተቀበሩ አስከሬኖችን ለማውጣት በሰው ሀይል ቁፋሮው እንደቀጠለ መሆኑንም ዛሬ የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለሸገር ተናግሯል፡፡

 

በአካባቢው ተጨማሪ አደጋ እንዳይደርስ ሰዎችን ድንኳን በመደኮን ወደ ሌላ አካባቢ የማስፈር ስራም እየተሰራ መሆኑን ሰምተናል፡፡


 

ትዕግስት ዘሪሁን

 


Comments


bottom of page