ሕወሀት ዳግም ተመዝግቦ ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው ዋጋ እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
“እኔ ብፈልግም ባልፈልግም ምርጫ ቦርድ ሕወሃትን ካልተቀበለው ፓርቲው ዋጋ የለውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው፡፡
ከትንሳኤ 70 እንደርታ ፓርቲ ተወክለው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከበደ አሰፋ የተባሉ የፓርቲው አባል “ሕወሃት ከልክ በላይ ወደ ዝርፊያ ገብቷል፣ አይበቃም ወይ” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“ሕወሃት በወርቅ ፣ በማዕድን እና በተለያዩ የብረታ ብረት ዝርፊያ ላይ ተሰማርቶ እራሱን እያጎለበተ በማን አለብኝነት ጉባኤ እንዳናደርግ የሚከለክለን ምድራዊ ሀይል የለም እያለ መግለጫ እያወጣ እንደ ትናንትናው ወደ ፉከራ እየገባ ነው” ብለዋል፡፡
“የጊዜያዊ አስተዳደሩ መከለስ የለበትም ወይ” ሲሉም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
“ሕወሃት ትጥቅ ፈትቶ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ወደ አካባቢው የሚገቡትስ መቼ ነው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ከዚህ ቀደም ምርጫ ቦርድ ምርጫውን አራዝማለሁ ሲል ብዙዎቻችን ስንስማማ ሕወሓት አልስማማም ብሎ የገባንበት ቀውስ ይታወሳል ብለዋል፡፡
ምን ያህል ሰው፣ ምን ያህል ሀብት እንደወደመ መገመት ትችላላችሁ ሲሉ ለተሳታፊዎች የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደመው የሰው እና ንብረትና ሀብት በትክክል ሳይገመገም እንዴት ጠፋ ሳይባል ሌላ ጥፋት ማምጣት ጥሩ አይደለም ሕዝብ ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እኛ ህጉን ያሻሻልነው ሕወሃትና መሰል ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ የሚያጣራውን አጣርቶ በተገቢው መንገድ እንዲፈቅድለት ዐቃቤ ህግ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ፅፈዋል ሲሉ ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
“አሁን ሕወሃት ማድረግ ያለበት በሁለት ሶስት ሳምንት ውስጥ የሚጠበቅበትን ዶክሜንት አሟልቶ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ነው ጉባኤ ማካሄድ ያለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
“ተመልሰን ጦርነት ውስጥ ከምንገባ ሕወሓት የቀረውን መስፈርት አሟልቶ በህጋዊ መንገድ ጉባኤ አካሄዶ ፓርቲውን ወደ ፖለቲካ ሥርዓት መመለስ ከሁሉም በላይ ሕወሃትን ሲቀጥል የትግራይን ሕዝብ ከዚያ ደግሞ እኛን ይጠቅማል” ሲሉ ዐቢይ አህመድ አስረድተዋል፡፡
ሕወሃት ከዚህ ቀደም እንደ አዲስ መመዝገብ ሳይሆን የምፈልገው ህጋዊ ሰውነቴ እንዲመለስልኝ ነው ምፈልገው ሲል መናገሩ ይታወሳል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments