የፍርድ ቤት እግድ ቢወጣም ሴቮር ሬስቶራንት እና ናታኒ ካፌ ታሸጉ፣ ቦታውም ታጠረ ሲል እንረዳዳ የሸማቾች ሕብረት ስራ ማህበር ተናገረ።
ማልማት እችላለሁ፣ ለቃችሁ ውጡ የተባላኩበትም አግባብ ልክ አይደለም በሚል፤ ሲከራከር የነበረው እንረዳዳ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሲያስተዳድራቸው የነበሩት ይዞታዎች ውስጥ ያሉ ካፌዎች መታሸጋቸውን፣ ቦታውም በቆርቆሮ መታጠሩን ተናገረ።
ማህበሩ ይዞታው እንዳይፈርስ በፍርድ ቤት እግድ ባስወጣም የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 አስተዳደር ግን ቤቶቹን ከማሸግ እና ከማጠር ወደ ኋላ አላለም ብሏል።
እንረዳዳ የህብረት ስራ ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የፊታችን ረቡዕ ቀጠሮ ተሰጥቶኝ ነበር ሲል አስረድቷል፡፡
ወረዳው የፍርድ ቤት እግዱን እንዲቀበልና እንዲያከብር ብንጠይቀውም እምቢ ብሏል ያሉት የማህበሩ አባላት ወረዳው ቤቶቹን ማሸጉንና ይዞታውን ማጠሩን ለሸገር ተናግረዋል፡፡
ሸገር በጉዳዩ ዙሪያ የቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 03 የጠየቅ ሲሆን ወረዳው ''ጉዳዩ እኔን አይመለከትም የሚለከተው ክፍለ ከተማውን ነው'' የሚል መስል አግኝቷል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ በበኩሉ ጉዳዩ ካቢኔ የወሰነበት በመሆኑ የእኛ ስራ ማስፈፀም ነው፤ ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚችለውም የመሬት አስተዳደር ነው የሚል መልስ ከቀናት በፊት ለሸገር ተናግሮ ነበር።
ማህበሩ ቦታዎቹን ከመንግስት የተረከበው በ1969 ዓ.ም መሆኑን ተናግሮ፤ ቦታዎቹም ከማዶ ሆቴል ጀርባ 2,700 ካሬ፣ ከደሳለኝ ሆቴል ጀርባ ደግሞ በድምሩ 8,100 ካሬ ሜትር መሆናቸውን ጠቅሷል።
‘’ሴቮር ሬስቶራንት’’ እና ‘’ናታኒ ካፌ’’ ያሉበትን ህንፃ ጨምሮ የሚያስተዳድረው ማህበሩ በድንገት ቦታውን እንድለቅ፣ ተከራዮቹንም እንዳስወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶኛል ማለቱ መዘገቡ ይታወሳል።
ቦታዎቹን የማልማት አቅሙ አለን፣ ቅድሚያ እድሉን ይሰጠን በሚልም ይመለከታቸዋል ያሏቸው ማነጋገራቸው ተናግረው ነበር።
Yorumlar