ሐምሌ 15፣ 2016 - የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቀበሌዎችን በማጠናከር ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እንደሚያሻሽል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሣ ተናገሩ
- sheger1021fm
- Jul 22, 2024
- 1 min read
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቀበሌዎችን በማጠናከር ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እንደሚያሻሽል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሣ ተናገሩ።
ወደ ከተማ የሚያድግ የክልሉ አካባቢ በመጪዎቹ አመታት እንደማይኖርም ርዕሰ መስተዳድሩ በአዳማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሣ የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2017ን ዕቅድ ለጨፌው አቅርበዋል።
ሪፖርቱን ተከትሎም የክልሉ ምክር ቤት ጨፌ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የመዋቅር ጥያቄዎች እና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በክልሉ የሚታዩ ችግሮች ከእነዚህ መካከል ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ምላሽ የክልሉ መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ቀበሌዎችን እንደሚያጠናክር ግን ደግሞ
ከተማ እንሁን የሚሉ ጥያቄዎችን ለመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት እንደማያስተናግድ ተናግረዋል።
አገልጋይ የሆነ መዋቅር በአንድ ጀምበር መፍጠር እንደማንችል እናውቃለን ያሉት ርዕስ መስተዳድሩ፤ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ግን ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች የአገልጋይነት ስሜት እንዲኖራቸው ከማድረግ በሻገር በቴክኖሎጂ የሚታገዝ ስርአት መዘርጋት፤
የሰዎችን እንግልት ለማስቀረት ወሳኝ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ በምላሻቸው ጠቅሰዋል።
የክልሉ አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይዘምን እንቅፋት ሆነው የታዩ ሞያተኞች እና የስራ ሃላፊዎች መግጠማቸውን አቶ ሽመልስ ለጨፌው አባላት ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ተከትሎ ጨፌው የቀረበለትን፤ የ2016 የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 ዕቅድን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
ንጋቱ ረጋሣ
Comments