በዚህ ዓመት 1,375 የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ተመዝግበው እየተወዳደሩ የነበረ ሲሆን፤ አሁን 400 የሚሆኑ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች መመልመላቸውን ሰምተናል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የተሻለ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው 50 ወጣቶች ውድድሩን ያሸንፋሉ፡፡
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የፈጠራ ስራ ሀሳብ ማበልፀጊያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አደሬ እንደሚሉት እንዲህ ዓይነት ውድድር መደረጉ ሀገሪቱ የራሳቸው ስራ የሚፈጥሩ ወጣቶች እንድታገኝ ይረዳታል፡፡
የስራ እና ክህሎት ያዘጋጀው የስራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ወጣቶች እየተወዳደሩበት ሲሆን 50 አሸናፊዎች ድጋፊ ተደርጎላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ይላሉ፡፡
ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ስራ ሲገቡ የፋይናንስ ችግር እንዳይገጥማቸው ከሽልማቱ ባለፈም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አብረውት እየሰሩ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር እየመከረበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው የጥቃቅንና አነስተኛ እስትራቴጂ ዘመኑን ያላገናዘበና አሁን ያለውን ቴክኖሎጂ የማይረዳ እስትራቴጂ ነበር የሚሉት አቶ ብርሃኑ አሁን የተዘጋጀው ፖሊሲ ይህን ችግር ይቀርፋል በማለት ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የስራ ፈጠራ ያላቸው ወጣቶች የሚያጋጥማቸው የፋይናንስ ችግር እና አላሰራ የሚሉ ፖሊሲዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ነው ያሉት ኃላፊው የተሻለ ስራ ለመስራት ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባል በማለት ይመክራሉ፡፡
በረከት አካሉ
Comments