ሐምሌ 14 2017 - የወራቶች እድሜ የቀረው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሁሉም ጦርነቶች ቆመው የሰላም ሂደት እንዲጀመር ኦፌኮ ጠየቀ
- sheger1021fm
- Jul 21
- 2 min read
Updated: Jul 22
ኢትዮጵያ ከባድ ሃገራዊ አደጋ ውስጥ ነች ያለው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ማካሄዱን ጠቅሶ ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ፓርቲው ትናንት ይፋ ባደረገው በዚሁ መግለጫ ህዝብ በተሰበረ የፖለቲካ ሂደት መቀጠል የለበትም ብሏል ኦፌኮ፡፡
መጭው ሃገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት መንግስት ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ይገባል ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝሯል፡፡
በቀዳሚነት የጠቀሰውም ሁሉም ጦርነቶች እንዲቆሙ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት እንዲጀመር የሚለው ነው፡፡
በኦሮሚያና አማራ ክልል ያሉ ግጭቶች አለም አቀፍ ታዛቢዎችም ቁጥጥር በሚያደረጉበት ሁኔታ በአስቸኳይ ቁመው ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
መንግስት የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በዘዴ አፍርሷል ሲል የሚከሰው ኦፌኮ ይህም ጋዜጠኞች፣ ማህበራዊ አንቂዎች እና የታዋቂ ፖለቲካ መሪዎችን ማሰር እና መሰወርን ያጠቃልላል ብሏል፡፡

በመሆኑም የዲሞክራሲ ነፃነቶች እንዲመለሱ እና የፓርቲውን አባላት ጨምሮ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን እና ሲቪል ማህበራት ላይ የወጡ አፋኝ ያላቸው የህግ ማዕቀፎችም እንዲሻሩ አሳስቧል፡፡
ያለማስፈራራትም በነፃ የመደራጀት የመሰብሰብና የመቀስቀስ መብትም በህግ የተፈቀደ ዋስትና እንዲሰጠው በመግለጫው መንግስትን ጠይቋል፡፡
ገለልተኛና እምነት የሚጣልበት የምርጫ ሂደት ይካሄድ ዘንድም ተቆጣጣሪው አካል ወይም ምርጫ ቦርድ በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት እና ግልፅ በሆነ መንገድ እንደገና እንዲዋቀር ኦፌኮ ጠይቋል፡፡
ይህም ሁሉን አቀፍ እና የህዝብ ውክልናን የሚያረጋግጥ የምርጫ ሥርዓት ለማምጣት በሚያስችል የምርጫ ህግ ማሻሻያ ላይ ከሚደረግ የሁሉምፓርቲዎች ስምምነት ጋር ሊያያዝ ይገባል ብሏል፡፡
እንዲሁም የመንግስት ተቋት ፣ የፍትህ አካላትና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በምርጫው ሂደት ፍጹም ገለልተኛ ሆነው እንዲያገለግሉ የሚያስችል ይፋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲኖረም ጠይቋል፡፡
የኢኮኖሚ ሉአላዊነትን እንዲመለስ በጠየቀበት ምዕራፍ ደግሞ ለከባድ እዳና ችግር ዳርገውናል ያላቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀየሩ ጠይቆ በምትኩ በምግብ ዋስትናና በስራ ፈጠራ ብዙሃኑን የሚጠቅሙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በኮሪደር ልማት ስም የሚካሄደው ቤት ፈረሳንም ህገ ወጥ ነው የሚለው ኦፌኮ ሰዎችን ማፈናቀል እንዲቆም አሳስቦ የኢኮኖሚ ፖሊሲውም ከገፅታ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተላቆ እንደ እርሻ ፣ ኢንዱስትሪ እና ንግድ ባሉ መሰረታዊ ዘርፍ ላይ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments