ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቀን ተተምኖ የሚመደበው ሂሳብ ማሻሻያ ከ2017 ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እያጠናቀቅሁኝ ነው አለ፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማር አንድ ተማሪ በቀን ለምግብ የሚታሰብለት ዋጋ 22 ብር ነው፡፡
በዚህ ዋጋ ቁርስ፣ ምሳውና እራቱን መመገብ ይቻል ተብሎ ተተምኖለታል፡፡
አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ይህ 22 ብር አንዳንድ አካባቢዎች የአንድ ሲኒ ሻይን ሂሳብን እንኳን መሸፈን አይችልም፡፡
በዚህም ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጨምሮ ዋጋ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል፡፡
ጊዜውን ያማከለ ትመና አይደለም የሚል ተቃውሞ ሲነሳ ይደመጣል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሁን ያለው የኑሮ ሁኔታ እና ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚመደበው የቀን ዋጋ ተመን አይመጣጠንም ይላሉ፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥናት እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን እስከ ነሃሴ ድረስ ስራዎች ተጠናቀው በአዲሱ የትምህርት ዘመን አዲስ የቀን ዋጋ ተመን ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዩኒቨርስቲ መምህራን ኑሮ ከብዷቸው ደሞዝ አንሷቸው በተጓዳኝ የጉልበት ስራ እየሰሩ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ ነው ይህንን ችግር ለመፍታት ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡
ከኮሚሽኑ ጋር በመሆን ጥናቶች እየተደረጉ ነው ያሉ ሲሆን እስከ ህዳር ድረስ ጥናቱ ይጠናቀቃል ያኔ አዲስ ነገር ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል አብዛኛው ክልሎች የመምህራን ደሞዝ መክፈል ተስኗቸው መምህራን ቅሬታ ሲያሰሙ ይደመጣል፡፡
ታዲያ ትምህርት ሚኒስቴር ይህ ችግር ክልሎች ለመምህራን ተብሎ የተሰጣቸው በጀት ለተባለው ጉዳይ ባለማዋላቸው እየተፈጠረ ያለ ችግር ነው ይላል፡፡
ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተነጋገረ ነው ተብሏል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ጥራት እንዲመጣ ከተፈለገ መምህራን ደሞዛቸው በጊዜ መከፈል አለበት ያለ ሲሆን አልያ ግን የታሰበው የትምህርት ጥራት ለማምጣት ያዳግታል ይላል፡፡
በረከት አካሉ
Comments