በተጠናቀቀው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 44 ሴት ተፈታኞች ፈተናውን እየወሰዱ መውለዳቸው ተሰማ፡፡
በዚህም ምክንያት ፈተናውን መጨረስ አልቻሉም የተባለ ሲሆን በመጭው ዓመት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ለፈተና እንደሚቀመጡ የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል ከ17,000 በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ቢመዘገቡም ፈተናውን ያልወሰዱ ናቸው ተብሏል፡፡
አብዛኞቹም የፀጥታ ችግር ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎች መሆናቸው ሰምተናል፡፡
2016 በተሰጠው የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወደ መፈተኛ ክፍል 354 ተማሪዎች ስልካቸው ይዘው ለመግባት ሞክረዋል ተብሏል።
ከዚህ ውስጥ 154 የሚሆኑት ከፈተና ጣቢያ እንዲወጡና ፈተናው እንዳይወስዱ መደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር ተናግሯል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ጣቢያ ሲያመሩ አደንዛዥ ዕፅ፣ ጥይት፣ ጫት፣ ሲጋራ እና ሌሎች የተከለከሉ ቁሶች ይዘው ተገኝተዋል ተብሏል።
እነዚህ ተማሪዎች ፈተናውን ቢወስዱም ውጤታቸው ይሰረዛል የተባለ ሲሆን፤ 12 የሚሆኑ ተማሪዎች በእቃ ስርቆትና በዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት ተይዘዋል።
በ2016 የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመፈተን 701,749 ተማሪዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን 684,372 የሚሆኑት ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸውን ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
17,371 የሚሆኑ ተማሪዎች ተመዝግበው ፈተናው ያልሰወዱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 9,152 የሚሆኑት አማራ ክልል ውስጥ ባሉ ግጭት ምክንያት ፈተናውን መውሰድ አልቻሉም ተብሏል።

በግጭት ምክንያት ፈተናውን ያልወሰዱ ተማሪዎች ሁኔታዎች ሲመቻች ትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች በማደራጀት ለተማሪዎች ፈተናውን ይሰጣል ሲሉ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስረድተዋል።
ዘንድሮ ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል 29,718 የሚሆኑት ተማሪዎች በበይነ መረብ የተፈተኑ ሲሆን ሀገሪቱ በዚህ መንገድ ፈተናውን የመስጠት አቅም እንዳላት ተረድተናል ይላሉ።
በሚቀጥለው ዓመት 50 ከመቶ የሚሆነው ተማሪ በበይነ መረብ ፈተናውን ይወስዳል የያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዚህ ዓመት የሚፈለገው ያህል ተማሪ በበይነ መረብ ያልተፈተኑት ክልሎች ምን ያህል ተማሪ በኦንላይን ፈተና እንደሚወስዱ ለዩኒቨርሲቲዎች ባለማሳወቃቸው ነው ተብሏል።
በዚህ ዓመት ከሚፈተኑ ተማሪዎች መካከል 1 ተማሪ በህመም ምክንያት ዋቻሞ ዩንቨርስቲ ላይ ሕይወቱ ሲያልፍ በአማራ ክልል ተፈታኞች ወደ ፈተና ጣቢያ ሲያመሩ በታጣቂዎች በተከፈተ ጥቃት 1 ተማሪና ሌሎች 2 ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው አጥተዋል።
3 ፈታኞች የፈተና ወረቀት በአግባቡ ባለመያዛቸው የተባረሩ ሲሆን ቁጥራቸው ያልተገለፀ ሌሎች ደግሞ ለተፈታኝ ተማሪዎች ስልክ ለማቀበል ሲሞክሩ ተይዘዋል ተብሏል።
በረከት አካሉ
Website: https://www.shegerfm.com/
Comments