top of page

ሐምሌ 11፣ 2016 - ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ማፅደቋ ስምምነቱ አለም አቀፍ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ ያስችላል ተባለ

ከ14 ዓመታት በላይ በድርድር ላይ የቆየው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ (The Nile Basin Cooperative Framework Agreement) ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ የሚያስችለውን ይሁንታ ከደቡብ ሱዳን አግኝቷል፡፡


ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ያስገኛል ያልናቸው የአባይ ጉዳይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ፈቅ አህመድ ነጋሽ፤ የደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ማፅደቅ ትብብሩን ያፀደቁ የአገራቱን ቁጥር ወደ 6 ከፍ ያደርገዋል ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ ህግ ሆኖ ለመፅደቅ ያስችለዋል ይላሉ፡፡


ይህ ስምምነት መፅደቁ በዋናነት ለኢትዮጵያ የሚኖረው ጥቅም ምንድነው? ከተባለ ትልቁና የመጀመሪያው ጥቅም ከአሁን በፊት በተፋሰሱ ውስጥ አገልግሎት ላይ የነበረውን የቅኝ ግዛትና ደህረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች ማለትም የ1929 እና የ1959ኙ ስምምነት በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ እንዲያጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል ተመራማሪው፡፡


ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞ ስምምነቶች የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት እንደ አገር መኖራቸውን የካደ ምንም ዓይነት የውሃ ድርሻ ያልሰጣቸው እንዲሁም በፈረሙ ሀገራት መካከል ኢ- ፍትሃዊ የሆነ የውሃ ድልድል እንዲኖር ያደረገ ነበር ሲሉ ፈቅ አህመድ ነጋሽ አስረድተዋል፡፡

ይሁንና የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ግን የተፋሰሱ ሀገራት ከዚህ በኋላ የሚያካሂዱት የውሃ አጠቃቀም ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው ያስችለዋል ተብሏል፡፡


ስምምነቱን 6ቱ ሀገራት ካፀደቁት የአፍሪካ ህብረት ከ2 ወር በኋላ አለም አቀፍ ስምምነት አድርጎ ያፀድቀዋል ተብሏል፡፡


ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ ተቋማት ብድር እንድታገኝ ሊረዳት እንደሚችል ፈቅ አህመድ ነጋሽ አስረድተዋል፡፡


የስምምነቱ መፀድቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት እኩል መብት የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ ቡድን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ናቸው፡፡


ሰብሳቢው የተፋሰሱ ሀገራት ከየትኛውም ተቋም ብድር እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ማፅደቋ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ሁነት ነው ሲሉ ትላንት በማህበራዊ ትስስር ገለፃቸው ባወጡት ፅሁፍ መናገራቸው ይታወሳል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page