''ከፍተኛ ክፍያ እኛ ሳንስማማ ጨምሯል'' በሚል ከተማሪ ወለጆች ቅሬታ የቀረበበት ''ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት'' ለ2017 የትምህርት ዘመን ምንም ጭማሪ እንዳያደርግ በመንግስት ታዘዘ።
ትዕዛዙን ያስተላለፈው የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ነው።
የቱርኩ ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፤
ለ2017 የትምህርት ዘመን የጨመረው ጭማሪ እና ጭማሪውን ያደረገበት መንገድ ትምህርት ቤቱትንና የተማሪ ወላጆችን አላግባባ ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።
ወላጆች ጭማሪ መደረጉን ያወቁት ለ2017 የትምህርት ዘመን ክፍያ ለመፈፀም በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ወደ ምህርት ቤቱ በሄዱበት አጋጣሚ መሆኑንን ነግረውናል፡፡
ጭማሪ ለማድረግ የትምህርት ዘመኑ ከማለቁ ሶስት ወር አስቀድሞ ከተማሪ ወላጆች ከ50 ከመቶ በላይ በተገኙበት፣የመንግስት ተወካይ ባሉበት ወይይይት ተደርጎ ስመምነት ላይ ከተደረሰ ነው ያሉት ወላጆቹ ክፍያ የተጨመረብን ግን ከእዚህ ህጋዊ አካሄዶች አንዱንም ሳይፈፅም ነው ብለው ነበር።
በማሪፍ ት/ቤት ላይ ሌላው ቀርቦ የነበረው ቅሬታም ክፍያው በዶላር ተቀምጦ በእለቱ ምንዛሬ ተመን በብር እንድንከፍል ተገርገናል ይህም ከህግ ውጪ ነው የሚል ነው።

ማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት በበኩሉ የክፍያ ጭማሪ ያደረገው ከተማሪ ወላጆች ጋር ተስማምቶ፣ህጉን ጠብቆ ለወላጆች ማሳወቁን ፣በስብሰባ ላይ ያልተገኙትን ግን ምንም ማድረግ አልችልም ብሎ መልስ ሰጥቶ ነበር።
በተማሪ ወላጆች እና በትምህርት ቤቱ መካከል መግባባት ባለመቻሉ መፍትሄው ከመንግስት እየተጠበቀ ነበር።
ጉዳዮ የሚመለከተው የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በዛሬው እለት ባወጣው ደብዳቤ የወላጆቹን ቅሬታ ተገቢ ነው ብሎ ትምህርት ቤቱ ጭማሪ እንዳያደርግ ወስኗል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጉዳዩ በንግግር እንዲፈታ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሶ ግን ሊሳካ አልቻለም ብሏል።
በመሆኑም የአለም አቀፍ፣ የማህበረሰብ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና የበጎ አድራጎት ት/ቤቶች ፈቃድ እና የፈቃደ እድሳት መመሪያ ላይ የትምህርት ቤት ክፍያን በተመለከተ የተቀመጠውን ጠቅሶ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስገድ ኢኮኖሚያዊ ምከንያት ካጋጠመ የትምህርት ዘመኑ ከመጠናቀቁ 3 ወራት ቀደም ብሎ ለወላጆች ማሳወቅ አለበት የሚለውን ባለመከተሉ፤ እንዲሁም ትምህርት ቤቱ ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት በዝርዝር በማቅረብ ከወላጅ ኮሚቴዎች እና ቢያንሰ ከ51% ከሚሆኑ ወላጆች ጋር በመወያየት የተደረሰበትን የስምምነት በቃለ-ጉባኤ የተደገፈ ሰነድ ለባለስልጣኑ ወይም ባለስልጣኑ ለወከለው አካል በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት የሚለውን ሙሉ በሙሉ ተቋሙ ባሉት ሁሉም ቅርንጫፎች በመመሪያው መሰረት አላሳወቀም ሲል መስሪያ ቤቱ አስረድቷል።
በዚህ ምክንያት ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ለ2017 የትምህርት ዘመን ክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችል የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አሳውቋል።
በተጨማሪም የትምህርት ቤት ከፍያን በዶላር ማስከፈል እንደማይቻል በ2013 የወጣውን የብሄራዊ ባንከ መመሪያ ትምህርት ቤቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
ንጋቱ ሙሉ
Kommentare