top of page

ሐምሌ 10፣ 2016 - በወንጀሎች ለተከሰሱ እና የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች መንግስት በነፃ ጠበቃ እንደሚያቆም ብዙ ሰዎች አያውቁም ተባለ

በተለያዩ ወንጀሎች ለተከሰሱ እና የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች መንግስት በነፃ ተከላካይ ጠበቃ እንደሚያቆም አሁንም ብዙ ሰዎች አያውቁም ተባለ።


መንግስት ይህንኑ አገልግሎት የሚሰጡ ዘጠና ተከላካይ ጠበቆችን እንደመደበ ሠምተናል።


ይህን አገልገሎት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር በተቋቋመው የተከላካይ ጠበቆች ፅህፈት ቤት አማካይነት እየሰጠ ይገኛል።


አገልግሎቱ የሚሰጠው ተከሳሾቹ በገንዘብ ችግር ምክንያት ያለ ጠበቃ ክርክር ቢያካሂዱ የፍትህ መጓደል ሊገጥም ይችላል ብሎ፤ ፍርድ ቤት ላመነባቸው ሰዎች ነው ሲሉ የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አቶ ደሳለኝ ከበደ ነግረውናል።


ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው 2106 በጀት ዓመትም በ13874 መዝገቦች በወንጀል ለተከሰሱ፤ ከ35,000 በላይ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች መንግስት በነፃ ተከላካይ ጠበቃ ማቆሙን ከአቶ ደሳለኝ ሠምተናል።


የፅህፈት ቤቱ 90 ተከላካይ ጠበቆች በሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሚገኙ 106 ችሎቶች አገለግሎቱን ሰጥተዋል ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል።


ይሁን እና ብዙ ሰዎች በመንግስት ወጪ በነፃ የተከላካይ ጥብቅና አገልግሎት እንደሚሰጥ አያውቁም ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል።


ወደፊት ግን የተቋሙ አገልግሎት ይበልጥ እየታወቀ መሄዱ ስለማይቀር እኛም ለዚሁ ራሳችንን እያዘጋጅን ነውም ብለዋል አቶ ደሳለኝ።


የጽህፈት ቤቱ ተከላካይ ጠበቆች ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በድሬደዋ፣ ሃዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ አሶሳ፣ ቡታጅራ፣ ወራቤ እና ግልገል በለስ ባሉ የፌዴራል ተዘዋዋሪ ችሎቶችም እየተገኙ አገልገሎቱን እየሰጡ ነው ተብሏል።




ንጋቱ ረጋሳ

Commenti


bottom of page