በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት ዓመትን ዕቅዳቸውን አዘጋጅተው ሳይጨርሱ በልዩ ፍቃድ ግዥ ለመፈጸም እየጠየቁ ነው ተባለ።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ግን ልዩ ፍቃድ የሚባል ነገር አይኖርም ብሏል።
#የፌዴራል_መንግስት_ግዥ_እና_ንብረት_አስተዳደር አዋጅ ባለፈው ወር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።
አዋጁ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ግዥ መፈጸም ያለባቸው በወረቀት አልባ ወይም ኤሌክትሮኒክ መላ ብቻ መሆን እንዳለበት ያዛል።
ግዢን ብቻ ሳይሆን የአመቱንም ዕቅድ ቀደም ብለው መስሪያ ቤቶቹ በኤሌክትሮኒክ መላ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል።
ይሁን እና በርካታ የመንግስት ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት አመትን ዕቅዳቸውን፤ አዘጋጅተው ሳይጨርሱ በልዩ ፍቃድ ግዥ ለመፈጸም እየጠየቁ ነው ተብሏል።
እንዲህ አይነቱ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ተናግሯል።
ዕቅድ ሳያዘጋጁ ግዥ የሚፈጽሙ ተቋማት ሃላፊዎች ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሀጂ ኢብሳ አስጠንቅቀዋል።
ለተለዩ እና በኤሌክትሪኒክ መላ ግዥያቸውን ማከናወን ለማይቻሉ ጥቂት ዘርፎች ብቻ ፍቃድ ልንሰጥ እንችላለን ብለዋል ዳይሬክተሩ።
የሚመደብላቸውን ተጨማሪ በጀት ላልታለመለት አላማ የሚያውሉ መስሪያ ቤቶች እንዳሉም ከ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም መረዳት ችለናል ያሉት አቶ ሃጂ ይህም ተቀባይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል።
ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተቋማቸውን ሁሉንም ፍላጎት ያካተተ እና ከተፈቀደው በጀት ጋር የተጣጣመ የግዥ ዕቅድ ፤ እስከ ሃምሌ 30/2016 አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መመሪያ እንዳስተላለፈ ሠምተናል።
ንጋቱ ረጋሳ
Comments