ሐምሌ 1 2017 - አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት ላይ እኩል ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም ተባለ
- sheger1021fm
- Jul 8
- 1 min read
ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ የተለያዩ ህጎችና ድንጋጌዎች ብታወጣም በአግባቡ የማይተገበሩ በመሆኑ አሁንም አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት ላይ እኩል ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም ተባለ፡፡
ይህንን ያስቀራል የተባለው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የተመለከቱ ህጎች በአንድ ተጠቃለው የሚገኙበት ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲና የአካል ጉዳተኞች አዋጅ ተሰናድቶ እየታየ ነው ተብሏል፡፡
የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ለማስከበር የወጡ ህጎች ቢኖሩም ስለ አፈፃፀማቸው በሚደረግ ማጣራት ግን አብዛኛዎቹ ተቋማት ተፈፃሚ እንደማያደርጉት አረጋግጫለሁ ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡
አቶ ሲሳይ ጥላሁን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚ ናቸው እርሳቸው እንደሚሉት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ የተመቹ ሆነው መገንባት ቢኖርባቸውም ይህንን የሚያሟሉት ግን ጥቂቶቹ ናቸው ይላሉ፡፡

አካል ጉዳተኞች የህንፃ ተደራሽነት ላይ ሰፊ ችግሮች ሲገጥማቸው እናያለን የሚሉት አቶ ሲሳይ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ በመንግስት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ላይ ሌሎች መዝናኛ ቦታዎች ከተደራሽነት አንፃር በተለይ የአሳንሰር አገልግሎት ክፍተት አለባቸው ብለዋል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የወጡ ህጎችን አፈጻጸማቸውን መከታተል የሚኒስቴሩ ሀላፊነት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ አሁንም ይህንን የተመለከቱና በተለይ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በአንድ አጠቃሎ የያዘ ፖሊሲና አዋጅ ተሰናድቶ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኞችን በተመለከቱ በርካታ ህጎች አሉና በአግባቡ ስለመተግበራቸው ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጨማሪ በተለይ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ሌሎችም አጥብቀው ሊሰሩበት የሚገባ ነው ሲሉ አቶ ሲሳይ ጠቅሰዋል፡፡
አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ህጎችን ጠቅልሎ ይዟል የተባለው ብሄራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ረቂቅ በ2015 ዓ.ም ሐምሌ ላይ ለፍትህ ሚኒስቴር ተልዕኮ ጥቅል አስተያየት ተሰጥቶበት ባለፈው አመት 2016 ዓ.ም ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments