ሐምሌ 1፣ 2016 - የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመማር ሌሎች ሀገራት እንደሚያደርጉት መግቢያ ነጥቡ ቀነስ ማድረግ የተሻለ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ
- sheger1021fm
- Jul 8, 2024
- 1 min read
የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመማር ከዚህ ዓመት ጀምሮ፤ እንደ ሀገር ወጥ የሆነ ፈተና በትምህርት ሚኒስቴር መሰጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ተማሪዎችም ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመቀጠል በትምህርት ሚኒስቴር የሚዘጋጀውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ ፈተና ወጥ በሆነ መንገድ መሰጠቱ ጥሩ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ተማሪዎቹ ሊማሩ የሚያመለክቱበት የትምህርት ክፍል የተለያዩ በመሆናቸው ወጥ ፈተና መሰጠቱ አግባብነት የለውም የሚሉ ባለሙያዎችም አሉ፡፡
በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና እና ትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በላይ ሀጎስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለሁሉም የድህረ ምረቃ ትምህርት ዓይነቶች የሚሰጠው የመግቢያ ፈተና ተመሳሳይ ነው ይላሉ፡፡
ነገር ግን በሌሎች አለማት በአንድ ዩንቨርስቲ ውስጥ ባሉ የትምህርት ክፍሎች የሚሰጠው የመግቢያ ፈተና እና የመቁረጫ ውጤት የተለያየ መሆኑን በመጥቀስ ለውጤታማ ትምህርት ከዛ ልምድ ቢወስድ መልካም ነው ይላሉ፡፡
የሚሰጠው የድህረ ምረቃ ፈተና በብዛት ተማሪው የማገናዘብ አቅም የሚፈትሽ በመሆኑ አሁን በወጥነት እየተሰጠ ያለው ፈተና ችግር አለው ማለት አይደለም ብለዋል፡፡
በድህረ ምረቃ የሚሰጠው ፈተና ከባድ ነው፤ ፈተናውን ማቅለል ይቻላል ይህ ግን መፍትሄ አይደለም ያሉት ዶክተር በላይ ፈተናው ከባድ እንዳለ ሆኖ ሌሎች ሀገራት እንደሚያደርጉት መግቢያ ነጥቡ ቀነስ ማድረግ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ፡፡
ለድህረ ምረቃ መግቢያ ፈተና በሌሎች አለማት የሚሰጠው በዩንቨርስቲዎች ውስጥ በየክፍሉ ሊለያይ ይችላል ያሉት ተመራማሪው ዶክተር በላይ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ከፈተናው ባሻገር የተማሪው የቀድሞ ውጤት እንደ መግቢያ የሚጠቀሙም አሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እራሳቸው በማጠናከር የየትምህርት ክፍላቸው መግቢያ ወጥ በሆነ መንገድ አፀድቀው ቢሰሩ የተሻለ ነው መባሉን ሰምተናል፡፡
በረከት አካሉ
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments