በኢትዮጵያ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እጥረት በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ችግሩ የሰፋ ነው ተባለ።
በሌላ በኩል ደግሞ የንፁህ ውሀ አቅርቦት ባለባቸው አካባቢዎች ብክነቶቸ እየታዩ መሆኑ ይነገራል፡፡
በተለይ በከተማ አካባቢ ችግሩ በስፋት እንደሚታይ ወተር ኤድ ኢትዮጵያ (Water Aid Ethiopia) ተናግሯል፡፡
በከተማ እና በገጠር አካባቢዎች ንፁህ ውሀ እና ሳኒቴሽን አገልግሎት እንዲያገኙ ለረጅም ዓመታት ሲሰራ የቆየው ወተር ኤድ ኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች ባሉ የውሀ አገልግሎቶች ብክነቶችን አስተውያለሁ ብሏል።
የንፁህ ወሀ አቅርቦት ከማስፋት በዘለለ በአገልግሎቶቹ አጠቃቀም ዙሪያ እየታየ ያለውን ችግሮች ለመቀነስ የሚረዳኝን የመጀመሪያ የሆነውን ደረጃውን የጠበቀ ሞጁል አሰናድቼ ወደ ስራ ልገባ ነው ብሏል፡፡
ወተር ኤድ ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የሚሰራቸው አገልግሎቶች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጉዳት እና የሀብት ብክነት ለመቀነስ ይረዳል ያለው የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሞጁል ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባር እንደሆነ የተናገሩት የዋተር ኤይድ ኢትዮጵያ የንጽህና ዘርፍ ማጠናከሪያ አማካሪ አቶ ሀይሌ ድንቁ ናቸው፡፡
የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሞጁሉ ሲዘጋጅ ከሁለት ዓመት በላይ ፈጅቷል ያሉት አቶ ሀይሌ በአለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ የስልጠና መመሪያ ሊኖረው የሚገባን ማንኛውንም ነገር አሟልቶ የተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ድርጅቱ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ላይ የምሰራቸው ፕሮጀክቶች አሉ ብሏል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው የሰላም እጦት ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ መቸገራቸውን ሸገር ሰምቷል፡፡
መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የንፁህ ውሀ አቅርቦት ለሟሟላት ስራዎችን እየከወኑ መሆኑ ይነገራል፡፡
ነገር ግን የንፁህ ወሀ አቅርቦት እጥረቱ በተለይ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ችግሩ ከፍተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Commentaires