top of page

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረውን መንግስት ለህዝብ ምሬት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ለማሻሻል ምን መስራት ይጠበቅበታል?

  • Jun 24
  • 2 min read

ሰኔ 17/2018


ባለፈው ወር በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያለው "ብልጽግና ፓርቲ" አሸናፊ መሆኑ ተነግሯል።


ፓርቲው ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ሀገሪቱን ለመምራት የሚያስችለውን መዋቅር ያደረጃል ተብሎ ይጠበቃል።


ለመሆኑ ፓርቲው የሚመሰርተው መንግስት ለህዝብ ምሬት መነሻ የሆኑና በተለይ በታችኛው መዋቅር የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ምን መስራት ይጠበቅበታል?


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 የተካሄደውን ሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ ውጤት ከሠሞኑ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።



በውጤቱም ምርጫ ከተካሄደባቸው 501 የፓርላማ የምርጫ መቀመጫዎች፤ 438ቱን በስልጣን ላይ ያለው ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉን አሳውቋል።


ፓርቲው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረውን መንግስት የመመሥረት መብት ማግኘቱን አረጋግጧል።


ፓርቲው የሚመሰርተው መንግስት የሚያዋቅረውን ቢሮክራሲ ተጠቅሞ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለህዝቡ ቃል የገባቸውን ፕሮግራሞች ለመተግበር መስራት እንደሚጠበቅበት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር ትምህርት ክፍል መምህሩ ጫላ ሃምቢሣ(ዶ/ር)ተናግረዋል።


ውጤቱ አሸናፊነትን ያጎናፀፈው ብቻ ሳይሆን ከባድ ሃላፊነትንም የጣለበት እንደሆነ ፓርቲው ማስታወስ አለበት ብለዋል።


አሸናፊ ፓርቲ መንግስት ሆኖ ለህዝብ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው መንገዶች አንዱ ሲቪል ሰርቪሱ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ጫላ ፤ በዚህ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ብቃትና ተነሳሽነት ጉዳይም ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ እንደሆነ ያነሳሉ።


ለአንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህብረተሰቡ አዎንታዊ አመለካከት እንደሌለው የሚናገሩት መምህሩ ፤ የዚህ መነሻው ኢ - ፍትሃዊነትና ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑ ነው ብለዋል።


ፓርቲው ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያለበት ይሄ አሉታዊ የሆነ አመለካከት እንዲቀየር ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል።


እነዚህ የፀጥታ ችግሮች ሰዎች ከቦታ ቦታ እንደ ልብ እንዳይዘዋወሩ፤ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም እንደተፈለገው እንዳይቀላጠፉ እንቅፋት መሆናቸው ይነገራል።


ይሄ የሠላም ችግር እንዲፈታም ማድረግ የሚቻለውም ጠንካራ መዋቅር በአሸናፊው ፓርቲ ሲደራጅ እንደሆነ ዶክተር ጫላ ጠቁመዋል።


ብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ መሆንን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በማስወገድና ፤ የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማዘመን እና ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በመከላከል፤ የተገልጋዩን ሕዝብ እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ለመስራት ቃል ገብቷል።


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….


ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page