ህዳር 6፣ 2017 - ለቀድሞዋ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ የምስጋና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው
- sheger1021fm
- Nov 15, 2024
- 1 min read
ለቀድሞዋ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ የምስጋና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
የምስጋና ፕሮግራሙን ያዘጋጁት በበጎ ፍቃድ የተሰባሰቡ ሴቶችና በሴቶች የሚመሩ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን ሰምተናል።
ዝግጁቱም ፕሬዝዳንቷ በስራ ዘመናቸው ላከናወኗቸው ስራዎች ምስጋና ለማቅርብ ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
የመጀመሪያዋ የኢፌዴሪ ሴት ፕሬዚዳንት የነበሩት ሳህለወርቅ ዘውዴ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውና በዲፕሎማትነታቸው የሴቶችን አመራር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ፣ የፆታ እኩልነት ለማስፈን እና ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው በዝግጅቱ ላይ ሲነገርላቸው ሰምተናል።
በተለይ በርካት ወጣት ሴቶች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ አስችሏል የተባለው ፕሬዚዴንሻል ኢኒሼቲቭ ፕሮግራም አበርክቶው የጎላ ሆኖ ሲጠቀስላቸው ሰምተናል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞዋን ፕሬዝዳንት የህይወት ታሪክ የተመለከተና በመቅዲ ፕሮዳክሽን የተዘጋጀ አጭር ዶክመንተሪ ፊልም ቀርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞዋን ፕሬዚዳንት እና ዲፕሎማት ሳህለወርቅ ዘውዴን በስራ አጋጣሚ የሚያውቋቸው አምሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ፣ ብሌን ወርቁ፣ ወ/ሮ ኢትዮጵያ ጥላሁን፣ ስኂን ተፈራ፣ ወ/ሮ ፅጌ ኃይሌ እና ሌሎች ምስክርነት ሰጥተዋል።
በሸራተን አዲስ በተካሄደው ዝግጅቱ ላይ አብረዋቸው የሰሩ ሰዎች ፣ የሴት ማሀበራት ተወካዮች ፣ ባለስልጣናት ፣ ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።

በ1942 በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት የቀድሞዋ ረዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ በጅቡቲ፣ በፈረንሳይ አምባሳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ተወካይ ሆነው ሰርተዋል።
በኬንያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው መስራታቸውም ይታወሳል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments