top of page

ህዳር 6፣2016 - ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በየወሩ 150 የቴሌኮም ማማዎችን እየገነባሁ ነው አለ

ኩባንያው ያለፉት 6 ወራት እቅድ አፈፃፀሙን በዛሬው እለት በዋና መስሪያቤቱ ለጋዜጠኞች አስረድቷል።


በዚህም ባለፉት 6 ወራት በቴሌኮም አገልግሎትም ሆነ በሞባይል ገንዘብ ዝውውር ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ሰምተናል።


ኩባንያው የገነባቸው የቴሌኮም ማማዎች 2,057 መድረሳቸው የተናገሩቱ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄሌፑት በየወሩም 150 ማማዎች እየገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


ከአንድ ዓመት በፊት የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የተናገረው ኩባንያው የቴሌኮም ደንበኞቹ ብዛት 4.1ሚሊዮን መድረሳቸውን ሰምተናል።


ባለፈው ነሃሴ ወር ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የወሰደው ኤምፔሳ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።


ከ12 የሀገር ቤት ባንኮች ጋርም ኤም ፔሳ አብሮ እየሰራ እንደሆነ ሲነገር ሰምተናል።


የኩባንያው አብዛኛው ወይንም 50 በመቶ ገቢ ከኢንተርኔት አገልግሎት መሆኑም ተነግሯል ።


ለቴሌኮም እና ለኤም ፔሳ ፍቃድ ከ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ መንግስት መክፈሉን ያስታወሰው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የ5 ዓመት እቅዱም 2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረግ እንደሆነ ዊል ቫንሄሌፑት ሲናገሩ ሰምተናል።

በመጪው 10 ዓመታት ውስጥም ከ 10,000 እስከ 12,000 የቴሌኮም ማማ የመገንባት እቅድ አለው ተብሏል።


የእስካሁኑ ጉዞዬ በጣም ጥሩ ነው ያለው ኩባንያው በአገሪቱ በተለይ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር የቴሌኮም ማማ ግንባታዬን አጓቶብኛል ብሏል።


ሳፋሪኮም፣ ኢትዮጵያ የመጣው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ፉክክር ለመግጠም ሳይሆን ዲጁታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰፋ ለማድረግ ነው ሲሉ ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።


ኩባንያው በ26 ከተሞች እየሰራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ ተደራሽነቱ 30 በመቶ ላይ ይገኛል ተብሏል።


የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የተሾሙት ዊም ቫንሄሌፑት ዜግነታቸው ቤልጂየማዊ ሲሆን ለ 20 ዓመታት ያህል የቴሌኮም ኩባንያዎች ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው መስራታቸውን ሲናገሩ ሰምተናል።


የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page