top of page

ህዳር 5፣2017 - የባሪያ ንግድ በህግ ጭምር ክልከላ ተጥሎበት የቀረ ጉዳይ ቢሆንም አሁንም መልኩን ቀይሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው ተባለ፡፡

  • sheger1021fm
  • Nov 14, 2024
  • 1 min read

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዛሬ ጀምሮ ባሰናዳው ለ2 ቀናት የሚዘልቀው  የታሪክ ሲምፖዚየም የባሪያ ንግድ በተለያዩ ሃገራት የነበረው መልክ እና እስካሁንም የቀጠሉ መዘዞችን በተመለከተ የተለያዩ ምሁራን የጥናት ፅሁፎችን አቅርበዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት የታሪክ መምህሩ እና ተመራማሪው ዶ/ር ተፈሪ መኮንን ባርነት ቀርቷል ቢባልም መልኩን ቀይሮ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ ፍትሃዊ ባልሆነ ሰፊ የኢኮኖሚ ልዩነት ፣ ሰዎችን በመሸጥና በማግለል እንዲሁም በተለያየ መገለጫ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ከሌላው ሃገር በተለየ በኢትዮጵያ የነበረው የባሪያ ንግድ ልዩ መልክ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡

እንደማሳያም በጎረቤት ኬኒያ ትውልዳቸው ከባሪያ የዘር ሐረግ ይመዘዛል የተባሉ ሰዎች ዜግነት እንደሚከለከሉ ፓስፖርትም ማውጣት እንደማይችሉ እና በብዙ ነገር የተገለሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግን ባሪያ በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ የነበረ እና ባሪያ የተባሉትም እንደ ቤት ውስጥ ሰራተኛ የሚቆጠሩና የባለፀጎች ወይም የባለስልጣናት አገልጋይ ሆነው በጊዜው ከነበረው ገበሬ የተሻለ ኑሮ ይኖሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲያውም ከጌቶቻቸው ጋር ትውልዳቸው በስልጣን ላይ የነበሩ እንደነበሩ በመጥቀስ አሁን እገሌ ከዚህ የዘር ሐረግ ይገኛል ተብሎ እንደሌላው ሀገር የመገለል ችግር ያለበትም አይደለም ብለዋል፡፡

ያም ሆኖ ፖለቲካው ታሪክን በተዛባ መንገድ መጠቀሚያ ስለሚያደርገው እና የባርነት ጉዳይ የኢትዮጵያን ባህልና አኗኗር በማያውቁ ነጮች በብዛት ተዛብቶ ስለተፃፈ ሐሰተኛ ትርክት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ተፈሪ መኮንን፡፡

ይህም አንዱን የማህበረሰብ ክፍል እና ሃይማኖት ገዥ ሌላውን ተገዥ አድርጎ በተዛባ መንገድ ለመፈረጅ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ ትዕግስት ዘሪሁን




 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page