ህዳር 30፣2017 - በኢትዮጵያ ከ81,000 በላይ በኤችአይቪ ኤድስ የተጠቁ ሰዎች ጤናቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አይታወቅም ተባለ
- sheger1021fm
- Dec 9, 2024
- 2 min read
በኢትዮጵያ በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች መካከል ከ81,000 በላዩ የት እንዳሉና ጤናቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አይታወቅም ተባለ፡፡
ይህ የተባለው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም በተካሄደውና ኢትዮጵያ በቫይረሱ ስርጭት ምን ደረጃ ላይ እንደሆነች ለማወቅ በተካሄደው ጥናታዊ ትንበያ ነው፡፡
በኢንስቲትዩቱ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 605,238 በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ይገኛል፡፡
ከእነዚህ መካከል 523,683ቱ ህክምና አግኝተው የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት እየወሰዱ ይገኛል፤ ቀሪዎቹ 81,555 የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይታወቅ እንጂ ወደ ህክምናም ይሁን መድሃኒት እያገኙ እንዳልሆነ ኢንስቲትዩቱ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
በኤችአይቪ ኤድስ ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል የሆነው AIDS HEALTH CARE FOUNDATION (AHF) የተባለውን ግብረ ሰናይ ድርጅት ስለ ጉዳዩ ጠይቀናል፡፡
አቶ ቶሎሳ ኦላና በፋውንዴሽኑ የኤች አይ ቪ መከላከል፣ ምርመራና ተያያዥ ስራዎችን የሚሰሩ ስራ ሃላፊ ናቸው፡፡
እርሳቸው ወደ ህክምና አልመጡም የተባሉትን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ91 ሺህ በላይ ያደርሱታል፡፡
እነርሱን አግኝቶ ማከምና የቫይረሱን መጠን በመድሃኒት መቆጣጠር ካልተቻለ ለምን ያህል ሰው ሊያዳርሱት እንደሚችሉ መገመት ይከብዳል ይላሉ፡፡
በዚህ አካሄድ እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጠር በ2030 ማለትም ከ5 ዓመት በኋላ ኤች አይ ቪን የማህበረሰቡ የጤና ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ከባድ ሊሆን እንደሚችልም ነግረውናል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በኤችአይቪኤድስ መከላከል ስራው እስከ ዛሬ 5 ዓመት ድረስ ለማሳካት ከተቀመጡት መካከል ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች መካከል 95 በመቶዎቹ ተመርምረው እራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ሲሆን በዚህ ኢትዮጵያ 90 በመቶ ላይ ደርሳለች ብሏል፡፡
ወደ ጤና ተቋም አልመጡም የተባሉት ከ81,000 በላይ ሰዎች ቀሪዎቹ 10 በመቶዎቹ እንደሆኑና በቀሩን ዓመታት እነዚህን ሰዎች አግኝተን ማከም ከቻልን ቫይረሱን የጤና ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በዘላቂ የልማት ግቦች የተቀመጠውን ማሳካት እንችላለን ያሉን በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ያደታ ናቸው፡፡
እንደ ሃገር በመከላከል ስራው ጥሩ ደረጃ ላይ ነን የሚሉት አቶ ፍቃዱ የስርጭት ምጣኔው ከፍ በሚልባቸው በከተሞች፣ በአፍላ ወጣቶችና በሴተኛ አዳሪ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጠንከር ያለ ስራ ይጠብቀናልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ከገጠር ይልቅ በከተሞች አካባቢ ያይላል በዚህም አዲስ አበባ በ3.25 በመቶ የስርጭት ምጣኔ ቀዳሚ ስትሆን የጋምቤላ ክልል በ3.24 በመቶ ይከተላል፡፡
በዚህ ላይ በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልገው ኮንዶም ከፍተኛ እጥረት መኖሩ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እያደረገው ነው፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments