top of page

ህዳር 3፣ 2017 - በኢትዮጵያ በስኳር ህመም ከሚያዙት ሰዎች መካከል 67 በመቶዎቹ ህመሙ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ጥናት አሳየ

በኢትዮጵያ በስኳር ህመም ከሚያዙት ሰዎች መካከል 67 በመቶዎቹ ህመሙ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ጥናት አሳየ፡፡


በአለም አቀፉ የስኳር ፌድሬሽን የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የስኳር ህመም አለባቸው፡፡


ከአጠቃላይ ህዝቡ 3.3 በመቶ የሚሆነው ለበሽታው ተጋላጭ ነው፡፡


ይሁንና የስኳር ህመም ቀድሞ ምልክት የማያሳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ በየጊዜው በህመሙ ከሚጠቁት ሰዎች 67 በመቶዎቹ ህመሙ እንዳለባቸው እንኳን እንደማያውቁ ጥናቱ አሳይቷል፡፡


በዓለም ዙሪያም 50 በመቶ ተጠቂዎች ህመሙ እንዳለባቸው አያውቁም ተብሏል፡፡


በአፍሪካ ደግሞ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ህመሙ ያለባቸው ሰዎች በህመሙ አንደተጠቁ አያውቁም ይላል ጥናቱ፡፡


በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ህመም ከተጠቁ 653 ሚሊዮን ሰዎች 80 በመቶዎቹ ኢትዮጵያ በምትመደብበት በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት የሚኖሩ መሆናቸውን ያስቀምጣል፡፡


ይሁንና የህመሙ ጥሩ ጎን ከ90 በመቶ በላይ ሰዎችን የሚያጠቃው ዓይነት 2 የሚባለው የስኳር ህመም ዓይነት ቀድሞ መከላከል የሚቻል መሆኑ ነው ያሉን የኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር ፕሬዝዳንትና በሙያቸውም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የውስጥ ደዌና የስኳር ህመም ስፔሻሊስት የሆኑት ጌታሁን ታረቀኝ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስኳር ህመም መድሃኒትም ሆነ ኢንሱሊን በከተማዋ ባሉ የመድሃኒት መደብርም ሆነ በመንግስት ተቋማት ማግኘት እንዳልቻሉ ብዙ ታካሚዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡


የፊታችን ሐሙስ ህዳር 5 የሚከበረውን የአለም የስኳር ህመም ቀንን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የጤና ሚኒስቴር ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ ምንም ዓይነት የስኳር መድሃኒትም ይሁን የኢንሱሊን እጥረት እንደሌለ ተናግሯል፡፡


እጥረቱ አርቴፊሻል ነው፣ በመንግስት በኩል ለ8 ወራት የሚሆን ክምችት አለ፣ በተለይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መድሃኒቱን በሚገባ እያገኙ ነው ብሏል፡፡


ከተቋቋመ ከ40 ዓመታት በላይ የሆነው ማህበራቸው በመላው ኢትዮጵያ ባለው 89 ቅርንጫፎቹ 20,000 ለሚሆኑ ለዓይነት 1 የስኳር ህመም ተጠቂዎች የመድሃኒት፣ የኢንሱሊንና የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ዶ/ር ጌታሁን ይናገራሉ፡፡


ስለ ስኳር ህመም ግንዛቤ የሚሰጥበት የአለም የስኳር ህመም ቀን የፊታችን ሀሙስ ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ መሰናዶዎች እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴርና የስኳር ህመም ማህበር በጋራ በሰጡት መግለጫ እወቁት ብለዋል፡፡


ምንታምር ጸጋው

Comments


bottom of page