top of page

ህዳር 3፣ 2017 - ''በትምህርት ፖሊሲዎች ዙሪያ ጥናት አድርገን ለፓርላማ አቅርበን ፓርላማውም ከተቀበለን በኋላ ምንም ታሳቢ ሳያደርጋቸው ወደ ጎን ትቷቸዋል'' ማህበሩ

‘’መንግስት በሚወጡ የትምህርት ፖሊሲዎች ዙርያ ግብዓቶችን እንዳቀርብ ይጠይቀኝና፤ ያቀረብኳቸው ግብዓቶች ግን በቅጡ ሳያያቸው ውድቅ ያደርጋቸዋል’’ ሲል የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማህበር ተናገረ፡፡


ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት በትምህርት ሚኒስቴር እና በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በኩል በሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ላይ ያለውን አተያይ እና የመፍትሄ ሀሳቦች ጥናት አድርጎ እንደሚያቀርብ ተናግሯል፡፡


‘’ነገር ግን እነዚህን በመንግስት ተጠይቆም ሆነ በራሱ ተነሳሽነት የሚያቀርባቸው ግብዓቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች በአግባቡ እንኳ ታይተው አያውቁም’’ ሲል ማህበሩ ዓመታዊ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ሲናገር ሰምተናል፡፡


የማህበሩ ፕሬዚደንት አረጋ ይረዳው(ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት በሚወጡ የትምህርት ፖሊሲዎች ዙሪያ ዘርፉን አይተን እና ጥናት አድርገን ለፓርላማ አቅርበን፤ ፓርላማውም ከተቀበለን በኋላ ምንም ታሳቢ ሳያደርጋቸው ወደ ጎን ትቷቸዋል ብለዋል፡፡

‘’የምናቀርባቸው ግብዓቶች ታሳቢም ሆነ ተግባራዊ የማይደረጉ ከሆነ የኛ ድካም ትርፉ ምንድነው?’’ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡


በተጨማሪም በትምህርት ሚኒስቴር እና በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በኩል ተናቦ የመስራት ክፍተት እንደሚያዩም አስረድረዋል፡፡


በማህበሩ የቀረበው ቅሬታን በተመለከተ ሸገር ራዲዮ በህዝብ ተወካዎች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ ስራ ስምሪት፣ ድልድል እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ታደሰ በዛ (ዶ/ር)ን ጠይቋል፡፡


ዶ/ር ታደሰ ‘’መንግስት ከዚህ በፊት ትኩረት ያደርግ የነበረው በራሱ የሚተዳደሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ነበረ፤ አሁን ግን የግሉንም በማካተት አዲስ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው’’ ብለዋል፡፡


የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሀገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፤ መንግስትም ይህንንይረዳል ብለዋል የቋሚ ኮሚቴው አባል፡፡


በሚወጡ የትምህርት ፖሊሲዎችና መመሪያዎች የግሎቹ ታሳቢ እንደሚደረጉ አስረድተዋል፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


bottom of page