ከተመሰረተ 30 ዓመት የሞላው ሕብረት ኢንሹራንስ "በ30 ዓመታት ታሪኬ ታላቅና አስደናቂ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ" አለ፡፡
ኩባንያው በ87 ባለሃብቶች፣ 25 ሚሊዮን የተፈረመ እና በ8.073 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የዛሬ 30 ዓመት ነው የተመሰረተው፡፡
ከ30 ዓመታት በፊት በአንድ ቅርንጫፍ ቢሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው #ሕብረት_ኢንሹራንስ በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ 70 ቅርንጫፎች አንዳሉት አስረድቷል፡፡
ኩባንያው ባለፈው የበጀት ዓመት ወደ 2 ቢሊዮን ብር የተጠጋ አረቦን መሰብሰብ ችያለሁ፣ ይህም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ከሚመሩት ሶስት ቀዳሚ ኩባንያዎች አንዱ ያደርገኛል ብሏል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተለያየ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ደንበኞች 693 ሚሊዮን ካሳ ከፍሎ ከግብር በፊት 612 ሚሊዮን ብር ትርፍ አግኝቻለሁ ሲልም አስረድቷል፡፡
ኩባንያው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለእያንዳንዱ አክሲዮን ከ 527 ብር በላይ የትርፍ ድርሻ ያከፋፈለ ሲሆን ይህም ከኢንዱስትሪው ከፍተኛው ነው ብሏል፡፡
ሕብረት ኢንሹራነስ የ30ኛ ዓመቱን የምስረታ በዓል እያከበረ ሲሆን የኩባያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሰረት ባዛብህ "ኩባንያው ያለፉትን 30 ዓመታት ወደ ታላቅነት የከፍታ ማማ የሚያወጡትን እልፍ ተግበራት አከናውኗል " ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ተግባራት መካከል በኩባንያው ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑትን ሴት ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደ አውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር በ2011 መምረጡን፣ ባለ 12 ፎቅ ሕንጻ ጨምሮ አራት የተለያዩ ሕንጻዎች በአዲስ አበባና በባህር ዳር መገንባቱን፣ ዘመኑን የሚመጥን፣ ቀላልና ከገጽታው ጋር አብሮ የሚሄድ አዲስ ኮርፖሬት ብራንድ ወደ ሥራ ማስገባቱን ስራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው የሸሪዓ መርሆዎችን የተከተለ የተካፉል ኢንሹራንስ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡
ሕብረት ኢንሹራነስ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ሲሆን ይህን የሚደረገውም ያለፈውን መዘከር መጪውን ለማስመር ስለሚያግዝ ነው ብሏል፡፡
የመስረታ በዓሉ በኢንዱስትሪው ውስጥ በጥሩ ክንውን መዝለቁን ለማውሳት፤ እዚህ ለመድረሱ ምክንያት የሆኑትን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለምሳሌ መስራች ባለአክሲዮኖች፣ ደንበኞች፣ የኢንሹራንስ ብሮከሮች፣ የሽያጭ ወኪሎች፣ ሰራተኞች፣ የስራ አጋሮች ለማመስገን፣ በደንበኞቹ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት ለማጽናት፤ ለመጪው ትውልድ የጉዞ ምዕራፎቹን ሰንዶ ለማስቀመጥ በማሰብ ነው ሲል ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስረድቷል፡፡
ሕብረት ኢንሹራንስ የባለአክሲዮኖች ብዛት 714 እንዲሁም የተፈረመ ከፒታሉ 1.5 ቢሊዮን ብር፣ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን ጠቅላላ ሃብቱም ብር 4.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
留言