top of page

ህዳር 28፣ 2015በዓረቦን ተመን ላይ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል የሚታየው ጤናማ ያልሆነ ፉክክር የኢንሹራንስ ዘርፉን እድገት እየጎዳው ነው ሲል ዓባይ

ህዳር 28፣ 2015


በዓረቦን ተመን ላይ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል የሚታየው ጤናማ ያልሆነ ፉክክር የኢንሹራንስ ዘርፉን እድገት እየጎዳው ነው ሲል ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ተናገረ።


በኩባንያዎቹ መካከል የተስተካከለ የመረጃ ልውውጥ አለመኖር፣ በዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ሀይል አለመኖር፣ የካፒታል መጠን ዝቅተኛ መሆን ሌሎች በማደግ ያለውን ዘርፍ እየጎዱ ያሉ ምክንያቶች መሆናቸውን ኩባንያው አንስቷል።


ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2014 በጀት ዓመት በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም ከጠቅላላ መድን ዋስትና ብቻ ከግብር በፊ 113.8 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ተናገሯል፡፡


ትርፉ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲመሳከር የ75.5 ሚሊዮን ብር ወይንም የ50.6 በመቶ እድገት እንዳለው ኩባንያው ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡


ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዓመታዊ የባለአክስዮኖች ስብሰባውን ህዳር 24፣ 2015 ዓ.ም አካሂዷል።


ኩባንያው በዓመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የ424.2 ሚሊዮን ብር አረቦን ማግኘቱን ተናግሯል።


ከዚህ ውስጥ 412.9 ሚሊዮን ብር የጠቅላላ መድን ድርሻ ሲሆን ቀሪው 11.3 ሚሊዮን ብር አረቦን የተገኘው ከሕይወት መድን ነው ተብሏል።


ከሕይወት መድን ዋስትና የተገኘው አረቦን ካባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ5 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየበሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡


ዓባይ ኢንሹራንስ በ2014 በጀት ዓመት ካገኘው ዓረቦን የተሽከርካሪ መድን ዋስትና ቀዳሚ ሲሆን 43.4 በመቶ ድርሻ ይዟል ብሏል።


ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ከኢንቨስትመንት 70 ሚሊዮን ብር አግኝቻለሁ ያለ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ50.2 እድገት አሳይቷል።


የኩባንያው የተጣራ የአረቦን ገቢም ባለፈው ዓመት ከነበረበት የ26.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 250.2 ሚሊዮን ብር መሆኑንን ከሪፖርቱ ላይ ተመልክተናል፡፡


ኩባንያው በዓመቱ ውስጥ ከጠቅላላ መድን ዋስትና የ134.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ካሣ ከፍያለው ብሏል፡፡


ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወይንም 73.6 በመቶው የተሽከርካሪ ዋስትና መሆኑ ተሰምቷል።


በዓመቱ ለህይወት መድን 4.3 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉን ተናግሯል።


ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጠቅላላ ሀብቱ 1.47 ቢሊዮን ብር፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 361 ሚሊዮን ብር ደርሶልኛል ብሏል፡፡


በ2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው 16.5 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ አስመዝግቧል፤ 60 በመቶውም የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ድርሻ ነው ተብሏል።


ከጠቅላላው የአረቦን መጠን 424.2 ሚሊዮን ብር ወይንም የ2.6 በመቶ የእኔ ድርሻ ነው ሲል ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሪፖርቱ ተናግሯል።


ንጋቱ ሙሉሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Comments


bottom of page