top of page

ህዳር 27፣2017 - በአፍሪካ የመጀመሪያው የኢትዮ ቻይና የፊልምና ቴሌቭዥን ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው ተባለ።

ይህ ፌስቲቫል ከፊታችን ታህሳስ 11 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ  የሚካሄድ ሲሆን አዘጋጁም ጎፋ ኢንተርቴመንት ከ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከባህልና ስፖርት ሚንስቴርና ከቻይና ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው ተብሏል።


ፌስቲቫሉ የ #ብሪክስ ሀገራት የፊልምና ቴሌቭዥን ፌስቲቫል ማስጀመሪያ ስለ መሆኑም አዘጋጆቹ ዛሬ ህዳር 27/2017 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።


በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ሰፊ ባህል ያላት ሀገር እንደመሆኗ የፊልም ኢንዳስትሪው  ረጅም ባለመጓዙ እንደ ቻይና  ካሉ ሌሎች የብሪክስ ሀገራት ተሞክሮ የምትወስድበትን መንገድ በመፍጠር በኩል የመክፈቻ ፌስቲቫል ይሆናል  ብለዋል።


የቻይና ኤምባሲ ካውንስለሯ ዣንግ ያ ዌይ በበኩላቸው በኢኮኖሚ የተሳሰረውን የሁለቱን ሀገር ዲፕሎማሲ በባህልና ኪነጥበብ በኩልም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር የታሰበ እና ቀጣይነት ያለው ፌስቲቫል እንደሆነ ተናግረዋል።


ታህሳስ 11 በሚጀምረው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው "ሂሩት አባቷ ማነው"ን ጨምሮ ከሁለቱም ሀገራት የተመራረጡ ታላላቅ ፊልሞች የሚታዩ ሲሆን የፓናል ውይይቶች እና ለሁለቱ ሀገራት የፊልም ኢንዱስትሪ የትውውቅ መድረክ የሚፈጥሩ ወርክሾፖች እንደሚቀርቡ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሰምተናል።


ንጋት መኮንን



Commentaires


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page