በአፍሪካ ሶስት ግዙፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ያገናኘ ስምምነት መደረጉ ተሰምቷል።
ስምምነቱ በባህር ውስጥ በተዘረጉ የፋይበር ኬብሎች ላይ በተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችና ግጭቶች ምክንያት ለሚደርሱ የአገልግሎት መቆራረጥ ችግሮች መፍትሄ ለማቀበል የሚያግዝ ብርቱ ፕሮጀክት ነው ተብሏል።
በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ በህብረት አንድ ጉዳይ ያገናኛቸው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች፤ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ቴሌኮሙኒኬሽን ግሩፕ መሆናቸውን ሰምተናል።
ኩባንያዎቹ አፍሪካን ከፍተኛ አቅም ባለው(multi-terabit) የየብስ ፋይበር ኮኔክቲቪቲ ለማስተሳሰር የሚያስችል የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ አብሮ ለመስራት የስምምነት ውል ቋጥረዋል።
ሶስቱ ቴሌኮም ኦፕሬተሮች እስከዛሬ የገነቡትን ልማድና ክህሎት እንዲሁም ያነጠፋትን መሠረተ ልማታቸውን በማናበብ የአፍሪካን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወደፊት ለማራመድ ለመምራት የሚያግዝ አንደኛው ምዕራፍ መሆኑን ሰምተናል።
የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፈጣን ባለከፍተኛ አቅም የመሬት ውስጥ የፋይበር ኔትወርክ አማራጭ ይሆናል ተብሏል።
በቀይ ባህር መስመሮች ላይ በሚደርስ አደጋ አህጉር አቀፍ ግንኙነቶች እንዳይቋረጡ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች አገልግሎት ሳይቋረጥባቸው እንዲዘልቁ ያግዛል መባሉን ሰምተናል።
ይህ ሶስቱም ኦፕሬተሮች ያደረጉት ስምምነት በአህጉር ደረጃ ድንበርን እልፍ ብሎ የቴክኖሎጂ መንገድ እንዲሰምር እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የምትራመድ አፍሪካን ለማየት እንደሚያግዝ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሰራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments