top of page

ህዳር 24፣2017 - በኢትዮጵያ በየዓመቱ 270 ሚሊዮን ኮንዶም የሚያስፈልግ ቢሆንም ወደ ሀገር እየገባ ያለው ከ90 ሚሊዮን ያልበለጠ መሆኑ ተነገረ

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 270 ሚሊዮን ኮንዶም የሚያስፈልግ ቢሆንም ወደ ሀገር ቤት እየገባ ያለው የኮንዶም መጠን ከ90 ሚሊዮን ያልበለጠ መሆኑ ተነገረ፡፡


ስለዚህም በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የ180 ሚሊዮን ያህል ጉድለት እንዳለ ያሳያል፡፡


የኤች አይቪ አድስ ቫይረስ (HIV AIDS) እና የአባላዘር በሽታዎችን ለመከላከል በሚል ጥቅም ላይ የሚውለው ኮንዶም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጥረት እንዳለ ሲነገር ይደመጣል፡፡


በጉዳዩ ዙሪያ በመስራት ላይ የሚገኘውና #የኮንዶም_ምርትን ወደ ሀገር ቤት እያስገባ በነፃ የሚያከፋፍለውን ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (AIDS HEALTH CARE FOUNDATION) የተባለውን ግብረ ሰናይ ድርጅት ጠይቀናል፡፡


አቶ ቶሎሳ ኦላና በፋውንዴሽኑ የኤችአይቪ መከላከል፣ ምርመራና ተያያዥ ስራዎችን የሚሰሩ የስራ ሃላፊ ናቸው፣ እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ በኮንዶም አቅርቦት የሚያስፈልጋት 270 ሚሊዮን ሆኖ እያለ መንግስትን ጨምሮ ድርጅታቸው እና ሌላውም ድርጅት ወደ ሀገር ቤት የሚስገባው ተዳምሮ በዓመት ከ90 ሚሊዮን አይበልጥም ብለዋል፡፡

በመንግስት ለ #በሽታ መከላከል ተብሎ አሁን ወደ ሃገር ቤት የገባው 55 ሚሊዮን ኮንዶም እንደሆነ መረጃው አለኝ የሚሉት አቶ ቶሎሳ ድርጅታቸው AIDS HEALTH CARE FOUNDATION 3 ሚሊዮን ኮንዶሞችን በየዓመቱ ያስገባል፤ ሌሎችም ግብረሰናይ ድርጅቶች የሚያቀርቡት ቫይረሱን ለመከላከል በቂ እንዳልሆነም ያነሳሉ፡፡


የኮንዶም ምርት ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ ከፍተኛ ታክስ ይታይባቸው ከነበሩ ምርቶች መካከል የነበረ መሆኑ በቂ ምርት እንዳይገባና እጥረት እንዲፈጠር፤ የገባውም ቢሆን ከፍ ባለ ዋጋ እንዲሸጥ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሆኑን የሚያነሱት የስራ ሃላፊው፤ ባሳላፍነው ሃምሌ 22 2016 ዓ.ም በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኮንዶም ወደ ሃገር ሲገባ ለጉምሩክ ይከፈል የነበረው 35 በመቶ #ታክስ ተነስቷል፤ በሽያጭ ወቅት የሚከፈለው የ15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስም ተነስቷል ብለዋል፡፡


ይህ በመሆኑ አስመጪዎች ምርቱን እንደልብ አምጥተው ለመለገስም ይሁን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ እድሉ አላቸው ብለውናል፡፡


የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2016 ዓ.ም በኤችአይቪ ዙሪያ ያደረገውና ኢትዮጵያ በቫይረሱ ስርጭትና መቆጣጠር ምን ደረጃ ላይ ናት የሚለውን በሚያሳየው ጥናታዊ ትንቢያ መሰረት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በቫይረሱ ከሚያዙት 7,428 ሰዎች መካከል ከ26 በመቶ በላዩን ድርሻ የሚይዙት ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች ናቸው፡፡


ድርጅታቸው ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽንም እነዚህ ሴቶች በሚገኙባቸው በትምህርት ቤቶች፣ በ #ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌላውም ስፍራ በተለይ የስርጭት ምጣኔው ከፍ በሚልባት አዲስ አበባ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ቶሎሳ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ እየተያዙ ካሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የአፍላ ወጣት ሴቶች የመያዝ ምጣኔ 1.7 በመቶ በመሆን አብላጫውን ቁጥር እየያዙ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2016 ዓ.ም ጥናታዊ ትንቢያ ያሳያል፡፡


የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የኤች ኤቪ ቫይረስ ስርጭት ባለፉት ዓመታት ከ1 በመቶ በላይ በመሆን ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ከነበረበት አሁን ወደ 0.8 በመቶ ማውረድ ተችሏል ብሏል፡፡


ስለሆነም የስርጭቱን መጠን ከዚህም ለመቀነስ ተለዋዋጭ የሆነውን የስርጭቱን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ የመከላከልና መቆጣጠር ስራዎች በመንግስት ይሰራልም ተብሏል።


ይሁንና ግብረሰናይ ድርጅት በሆነው AHF የኤች አይ ቪ መከላከል፣ ምርመራና ተያያዥ ስራዎች የስራ ኃላፊው አቶ ቶሎሳ ኦላና ለቫይረሱ መከላከል ስራ ዋነኛ ግብዓት የሆነው ኮንዶም እጥረት ካልተፈታና በዚህ ከቀጠለ ወደ ነበርንበት ልንመለስ እንችላለን ሲሉ ስጋታቸውን ነግረውናል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page