top of page

ህዳር 23፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሪክስ አባል አገሮች በአለም አቀፍ ንግድ በዶላር ከመገበያየት ካፈነገጡ በእጥፍ የቀረጥ ታሪፍ እቆልልባቸዋለሁ አሉ፡፡


ሙከራም ለቀረጥ ቁለላ እንደሚዳርግ ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የብሪክስ አባል አገሮች በአለም አቀፍ የንግድ ክንውናቸው ራሳቸውን ከዶላር የማራቅ ጥረት መጀመራቸው ይነገራል፡፡


ብራዚል ፣ ሩሲያ ፣ ሕንድ ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ነባር የብሪክስ አባል አገሮች ናቸው፡፡

ዘግየት ብለው ደግሞ ኢራንን ፣ ግብፅን ፣ ኢትዮጵያን እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን አባል አድርጓቸዋል፡፡


ትራምፕ የብሪክስ አባል አገሮች ራሳቸውን ከዶላር የሚያርቁበትን እርምጃ እጃችንን አጣጥፈን አናይም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የትራምፕን የቀረጥ ቁለላ ዛቻ በተመለከተ ከብሪክስ አባል አገሮች በኩል ፈጥኖ አስተያየት የሰጠ የለም፡፡



በናይጀርያ ኮጊ ግዛት በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ በጥቂቱ የ27 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡


አደጋው በኒጀር ወንዝ የደረሰው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


ቢቢሲ ደግሞ እስከ ትናንት ምሽት የአደጋው ሟቾች ብዛት ከ50 በላይ መድረሱን ዘግቧል፡፡


አደጋ የገጠማት ጀልባ ከ200 በላይ መንገደኞችን አሳፍራ ነበር ተብሏል፡፡


ጀልባዋ ለመጥፎ እጣ የተዳረገችው ከኮጊ ወደ ኒጀር ግዛት በማምራት ላይ በነበረችበት ወቅት ነው፡፡


በአደጋው ከ150 የማያንሱ ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ ተጠቅሷል፡፡


በናይጀሪያ ባለፈው ወርም አንዲት የመንገደኞች ማጓጓዣ ጀልባ ተገልብጣ በመስጠሟ የ200 ያህል ሰዎች ሕይወት ማለፉን መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ልጃቸው ሐንተር ባይደን ፈፅሟቸዋል በተባሉ ወንጀሎች በህግ እንዳይጠየቅ ፕሬዘዳንታዊ ይቅርታ አደረጉለት ተባለ፡፡


ሐንተር ባይደን በህገወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በመያዝ እና በግብር ስወራ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን CNN አስታውሷል፡፡


እንደውም ቀደም ሲል በተከሰሰባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን በቅርቡም የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍበት ነበር ተብሏል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ያደረጉለት ሙሉ ይቅርታ የቅጣት ውሳኔውንም ሆነ መታሰሩን እንደሚያስቀርለት ተጠቅሷል፡፡


ጆ ባይደን በመግለጫቸው ቀድሞ ነገር ልጄ እንዲከሰስ ያደረጉት በፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንዳልወዳደር ያደቡ የፖለቲካ ተቀናቃኖቼ ነበሩ ብለዋል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ልጃቸው በህግ እንዳይጠየቅ ሙሉ ቅርታ ያደረጉለት ሀላፊነታቸው ለተመራጩ ዶናልድ ትራፕ ለማስረከብ ከወር ተኩል ያነሰ ጊዜ በቀራቸው አጋጣሚ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


bottom of page